የሀገር ውስጥ ዜና

ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥ አደጋዎችን በመቋቋም ረገድ አርአያ የሚሆን ሥራ እያከናወነች ነው – አቶ አደም ፋራህ

By Melaku Gedif

July 31, 2025

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 24፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በም/ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ኃላፊና የብልጽግና ፓርቲ ም/ፕሬዚዳንት አደም ፋራህ በአንድ ጀንበር የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር በጅግጅጋ ከተማ ችግኝ ተክለዋል፡፡

አቶ አደም በዚህ ወቅት እንዳሉት ÷ በዛሬው ዕለት እየተከናወነ በሚገኘው የአንድ ጀንበር የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር መላ ኢትዮጵያውያን እየተሳተፉ ይገኛሉ፡፡

የአረንጓዴ ዐሻራ ዘርፍ ብዙ ጠቀሜታ እንዳለው ገልጸው ÷ ሕዝቡም የመርሐ ግብሩን ፋይዳ በሚገባ እየተገነዘበ መምጣቱን አመልክተዋል፡፡

አረንጓዴ ዐሻራ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ፣ ለሥራ እድል ፈጠራ፣ ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ እንዲሁም የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት አውስተዋል፡፡

ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥ አደጋዎችን በመቋቋም ረገድ በአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር አርአያ የሚሆን ሥራ እያከናወነች እንደምትገኝም አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡

ኢትዮጵያ በችግኝ ተከላ በየዓመቱ የራሷን ሪከርድ እያሻሻለች መሆኑን ጠቁመው ÷ ይህም ለሀገራችን ብቻ ሳይሆን ለመላው ዓለም ጉልህ ፋይዳ እንዳለው አስረድተዋል፡፡

አቶ አደም ፋራህ ሕብረተሰቡ በአንድ ጀንበር የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር በንቃት እንዲሳተፍም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

በመላኩ ገድፍ

#አረንጓዴዐሻራ

#GreenLegacy