አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 24፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር የኢትዮጵያ ሁለንተናዊ ዕድገት ዘላቂ እንዲሆን ያስችላል አሉ በሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት የመንግሥት ዋና ተጠሪ ሚኒስትር ተስፋዬ በልጅጌ (ዶ/ር)፡፡
የሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት አመራሮች፣ የም/ቤቱ ጽ/ቤት አመራሮች እና የጽ/ቤቱ ሠራተኞች በአንድ ጀንበር የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር ችግኝ ተክለዋል፡፡
ሚኒስትሩ በዚህ ወቅት እንዳሉት ÷ የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር የኢትዮጵያ ሁለንተናዊ ዕድገት ዘላቂ እንዲሆን የሚያስችል ነው፡፡
የአረንጓዴ ዐሻራ የኢትዮጵያ ዕድገት ከተፈጥሮ ጋር የታረቀ እንዲሆን ትልቅ አስተዋጽኦ እያበረከተ እንደሚገኝም አብራርተዋል፡፡
መርሐ ግብሩ በአካባቢ ጥበቃ እና የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ በሚደረገው ርብርብ አበረታች ውጤት ማስገኘቱን ነው ያስገነዘቡት፡፡
የአረንጓዴ ዐሻራ በዓለማችን አሳሳቢ የሆነውን የአየር ንብረት ለውጥ ለመከላከል የራሱን አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡
በአንድ ጀንበር 700 ሚሊየን ችግኞች የመትከል መርሐ ግብር ኢትዮጵያ ለአፍሪካ ሀገራትና ለዓለም ልምድ የሚቀሰምበት ተግባር እያከናወነች ነው ብለዋል፡፡
የዚህ ታሪክ አካል የመሆን ዕድል ያገኙ ኢትዮጵያዊያን ችግኞችን በመትከልና የተተከሉትን በመንከባከብ የተሻለች ሀገርን ለትውልድ ለማስተላለፍ የበኩላቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል፡፡
#አረንጓዴዐሻራ #GreenLegacy