default

የሀገር ውስጥ ዜና

በአንድ ቀን 700 ሚሊየን ዛፎችን ለመትከል ያቀድነው ዕቅድ ከታሰበው በላይ ተሳክቷል – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)

By Mikias Ayele

July 31, 2025

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 24፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በአንድ ቀን 700 ሚሊየን ዛፎችን ለመትከል ያቀድነው ዕቅድ ከታሰበው በላይ ተሳክቷል አሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት÷ ኢትዮጵያውያን ሲተባበሩ ተአምር እንደሚሠሩ ዛሬ ዳግም ታይቷል ብለዋል፡፡

“በመትከል ማንሠራራት” በሚል መሪ ቃል በአንድ ቀን 700 ሚሊየን ዛፎችን ለመትከል ያቀድነው ዕቅድ ከታሰበው በላይ ተሳክቷል ነው ያሉት።

አመራሮችና ሠራተኞች፣ የግልና የመንግሥት ተቋማት፣ ኤምባሲዎች እና ዓለም አቀፍ ድርጅቶች፣ ሕጻናት፣ ወጣቶች፣ ጎልማሶች፣ አረጋውያን፣ ወንዶችና ሴቶች ለአረንጓዴ ዐሻራ ዛሬ በማለዳ፣ ከወፎች ቀድመው ወጥተዋል ሲሉም ተናግረዋል።

አረንጓዴ ዐሻራ የኢትዮጵያውያን ባህል እየሆነ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) ÷ የኢትዮጵያን መልክም እየቀየረ ነው፤የኢትዮጵያን ታሪክም እየቀየረ ነው፤ የዓለምንም መልክ እየቀየረ ነው ብለዋል።

ይሄንን ተልዕኮ ያስተባበሩትን እና የቀረበውን ጥሪ ሰምተው ወጥተው የተከሉትን ሁሉም አመስግነዋል፡፡

ኢትዮጵያውያን ፣ ትውልደ ኢትዮጵያውያን እና የውጭ ዜጎች በብዛት እና በምልዐት ስላደረጉት ተሳትፎ በኢትዮጵያ ስም ምስጋና አቅርበዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ መትከል ለልጆቻችን ጥላ መዘርጋት ነው ሲሉም አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡