የሀገር ውስጥ ዜና

በክልሉ ለሚነሱ የልማትና መልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ምላሽ መስጠት ይገባል

By Adimasu Aragawu

August 01, 2025

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 25፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በክልሉ የተገኘውን ሰላም በማስጠበቅ በህዝቡ ለሚነሱ ልማትና መልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ምላሽ ለመስጠት ጠንክሮ መስራት ይገባል አሉ የጋምቤላ ክልል ምክር ቤት አፈ ጉባኤ መሰረት ማቲዎስ።

የክልሉ ምክር ቤት 6ኛ የምርጫ ጊዜ 4ኛ የስራ ዘመን 8ኛ መደበኛ ጉባኤውን ዛሬ በጋምቤላ ከተማ መካሄድ ጀምሯል።

የምክር ቤቱ አፈ ጉባኤዋ መሰረት ማቲዎስ ጉባኤውን ሲከፍቱ እንዳሉት÷ በክልሉ የተገኘውን ሰላም በማጽናት ለህዝቡ የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት ሁሉም በአንድነት ጠንክሮ ሊሰራ ይገባል።

በተለይም የግብርና ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ በኩል ትኩረት ሰጥቶ መስራት እንደሚገባ ተናግረዋል።

በክልሉ የስራ እድል ፈጠራ ሥራዎችን ይበልጥ በማጠናከር የወጣቱን ተጠቃሚነት በማረጋገጥ በኩልም ሌላው በትኩረት ሊሰራበት የሚገባ ጉዳይ መሆኑን አንስተዋል።

በበጀት ዓመቱ ምክር ቤቱ በክልሉ የታለሙ የልማትና የመልካም አስተዳደር እቅዶች ስኬታማ እንዲሆኑ የተጠናከረ ክትትልና ድጋፍ በማድረግ የህዝቡ የልማት ፍላጎቶች ምላሽ እንዲያገኙ ያላሰለሰ ጥረት ማድረጉን አውስተዋል።

በቀጣይ የተጀመሩ የድጋፍና ክትትል ስራዎችን በማጠናከር በህዝቡ የሚነሱ የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ምላሽ እንዲያገኙ ምክር ቤቱ በትጋት ይሰራል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

ጉባኤው ዛሬን ጨምሮ በሚኖረው የሁለት ቀናት ቆይታ የክልሉን የ2017 የልማትና የመልካም አስተዳደር፣ የኦዲትና የጠቅላይ ፍርድ ቤት የእቅድ ክንውን ሪፖርት በማድመጥና በመወያየት እንደሚያጸድቅ ይጠበቃል።

እንዲሁም የ2018 እቅድ፣ የማስፈጸሚያ በጀት፣ አዋጆችንና ሌሎች ጉዳዮች ላይ ውይይት በማድረግ ውሳኔዎችን እንደሚያሳልፍ ተመላክቷል።

ፈጣን እና ወቅታዊ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

YouTube www.youtube.com/@fanamediacorporation Facebook www.facebook.com/fanabroadcasting Telegram t.me/fanatelevision Website www.fanamc.com TikTok www.tiktok.com/@fana_television WhatsApp www.whatsapp.com/channel/0029VbB0dRxG8l59MUkoWR29 Amharic Entertainment YouTube www.youtube.com/@fanaentertainment Facebook www.facebook.com/wmccwaltamediaandcommunicationcorporate TikTok www.tiktok.com/@fanamc_entertainment Amharic Documentary YouTube www.youtube.com/@fanamcdocumentary በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡ ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስለሆኑ እናመሰግናለን!