አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 25፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ከተማዋን ከታሪኮቿ ጋር እያጣጣምን ዘመናዊ ከተማ እያደረግናት እንገኛለን አሉ፡፡
ከንቲባዋ በዛሬው ዕለት 4 ኪሎ ፕላዛን፣ 4 ኪሎ የገበያ ማዕከልን እና መኪና ማቆሚያን መርቀው ለአገልግሎት ክፍት አድርገዋል።
የሀገራችን ብሎም የከተማችን አበይት ታሪካዊና የድል ሀውልታችን መገኛ የሆነውን የ4 ኪሎ አደባባይ አካባቢን ግዙፍ ታሪኩን በሚመጥን አግባብ ገንብተን ለአገልግሎት ክፍት አድርገናል ነው ያሉት።
ዛሬ ተመርቆ ለአገልግሎት ክፍት የሆነው ፕሮጀክቱ ከመሬት በታች የተገነቡ ዘመናዊ 102 የስጦታና የአልባሳት መደብሮች፣ ካፍቴሪያዎች፣ ማንበቢያ ስፍራዎች፣ ሱፐር ማርኬቶችን ያካተተ ነው፡፡
በተጨማሪም ከ100 በላይ ተሽከርካሪዎችን በአንድ ጊዜ የሚያስተናግድ የመኪና ማቆሚያና በአንድ ጊዜ እስከ 5 ሺህ ሰዎችን መሰብሰብ የሚያስችል የፕላዛ፣ የአንፊ ቴአትርና የተለያዩ የጥበብ ስራዎችን ማቅረቢያ ስፍራዎችን የያዘ መሆኑንም ከንቲባዋ የገለጹት፡፡
የሲቪል ተሳትፎን፣ የባህል ዕድገትን፣ የእግር ጉዞን የሚያበረታታ፣ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የታገዘ፣ ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍል በተለይም አቅመ ደካሞችና አካል ጉዳተኞችን ታሳቢ ያደረገ ነው ብለዋል።
ፕሮጀክቱ ከወዲሁ ከ500 በላይ ለሚሆኑ ወጣቶችና ሴቶች የስራ ዕድል መፍጠሩን ጠቅሰው፥ የቱሪዝም ፍሰቱን በመጨመር ለዘርፉ ዕድገት የራሱ ጉልህ አስተዋጽኦ ይኖረዋልም ነው ያሉት፡፡
በታለመለት ልክ እንዲጠናቀቅ ድጋፍና ክትትል ሲያደርጉ ለነበሩ አካላትና ለአካባቢው ማህበረሰብ ምስጋና ማቅረባቸውን የከተማ አስተዳደሩ የኮሙኒኬሽን ቢሮ ለፋና ዲጂታል ገልጿል፡፡