የሀገር ውስጥ ዜና

የሳይንስ ሙዚየም ቋሚ ኤግዚቢሸን ያለፈውን የያዘ፤ የሚመጣውን ያለመ ነው – አቶ ደስታ ሌዳሞ

By Mikias Ayele

August 03, 2025

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 27፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የሳይንስ ሙዚየም ቋሚ ኤግዚቢሸን ያለፈውን ጊዜ በታሪክነት የያዘ፤ የሚመጣውን አሻግሮ ያለመ ነው አሉ የሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ደስታ ሌዳሞ፡፡

የብልጽግና ፓርቲ ምክር ቤት አባላት ከእንጦጦ እስከ 4 ኪሎ ፕላዛ፣ የሳይንስ ሙዚየም ቋሚ ኤግዚቢሽንና መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎትን ጎብኝተዋል፡፡

አቶ ደስታ ሌዳሞ በጉብኝቱ ወቅት እንዳሉት፤ የአዲስ አበባ የኮሪደር ልማት የከተሞችን ትንሳኤ ያበሰረ ነው፡፡

ከተሞች ለነዋሪዎቻቸው ምቹ እና ለኢንቨስትመንት ሳቢ ለማድረግ እየተከናወኑ የሚገኙ ተግባራት ውጤታማ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

ከእንጦጦ እስከ 4 ኪሎ ፕላዛ የተከናወነው የኮርደር ልማት ስራም ድንቅ እና አዲስ አበባ እንደ ስሟ እያበበች ለመሆኗ ትልቅ ማሳያ ብለዋል።

የሳይንስ ሙዚየም ቋሚ ኤግዚቢሽን ዜጎችን ለመጪው ዓለም የማዘጋጀት ተልዕኮ ማንገቡን ጠቁመው፤ ኢትዮጵያ ሳይንስና ቴክኖሎጂን በላቀ ደረጃ ለመጠቀም ያላትን ጽኑ ፍላጎት የሚያሳይ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ቋሚ ኤግዚቢሽኑ በአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ፣ በአየር ንብረት ለውጥ የኢትዮጵያ ምላሽ፣ በግብርና፣ በውኃ ኃይልና ኢነርጂ እንዲሁም አቪየሽንና በሌሎችም ዘርፎች ላይ ያተኮሩ ዐውደ ርዕይ መያዙንም ገልጸዋል፡፡

ወጣቱ ቴክኖሎጂን በመጠቀም የፈጠራ ስራን እንዲያጎለብት የሚያነሳሳና ትውልዱ ለሚመጣው ተግባር ራሱን የሚያዘጋጅበት ዘመኑን የዋጀ መሆኑንም መግለጻቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

ዘመኑን የዋጀ ቴክኖሎጂን አቀናጅቶ የያዘው መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ለተገልጋዩ ቀልጣፋ አገልግሎት መስጠት የሚችል ትልቅ ተቋም ነው ብለዋል።