አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 28፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) በብዝኃ ቋንቋ ከኢትዮጵያ አልፎ አፍሪካን ለዓለም ለማሳየት የያዘው ግብ የሚደነቅ ነው አሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ፡፡
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሑፍ÷የኢትዮጵያን አቋም ካለፉት 82 ዓመታት በላይ በማይናወጥ መልኩ ለዓለም ያስተጋባውን የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ዛሬ ጎብኝተናል ብለዋል፡፡
ኢዜአ ዛሬ ወደ አዲስ ምዕራፍ ተሸጋግሯል፤ ታሪካዊ ዐሻራውን በአዲስ እሳቤ እያዳበረ ለሥራ ምቹ የሆነ ከባቢን፣ ዘመናዊ የሚዲያ ኮምፕሌክስና ዘመናዊ ስቱዲዮዎችን ገንብቷል ነው ያሉት፡፡
በዚህም የመጪው ዘመን ቀንዲል ሆኖ ለማገልገል በብዝኃ ቋንቋ ከኢትዮጵያ አልፎ አፍሪካን ለዓለም ለማሳየት የያዘው ግብ የሚደነቅ መሆኑን አውስተዋል፡፡
የሚዲያ ተቋሙ ሀገራዊ ጥቅሞችን እያስጠበቀ፣ የባህልና የቱሪዝም ሃብቶችን እያስተዋወቀ፣ መልካም ገፅታችንን ለዓለም እያሳየ ለመቀጠል በሰው ኃይልና በሚዲያ ቴክኖሎጂ ራሱን እያደራጀ መሆኑ ይበል የሚያሰኝ ጅምር እንደሆነም አንስተዋል፡፡
በተለይ በውጭ ቋንቋዎች (Pulse of Africa) የአፍሪካ ድምጽ ለመሆን የጀመራቸው እንቅስቃሴዎች ተጠናክረው ሊቀጥሉ እንደሚገባ አመልክተዋል፡፡
የአፍሪካን የወደፊት ዕጣ ፈንታ ራሳችን ተልመን፣ ራሳችን ሰርተን፣ ራሳችን ጽፈን፣ ራሳችን ለዓለም የምንናገረውና የምናሳየው መሆን ይኖርበታል ሲሉም አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡
ለዚህ ደግሞ መንግስት ተቋሙ የጀመራቸውን ሀገራዊ እና አህጉራዊ የለውጥ አራማጅ ግቦች ለማሳካት በቁርጠኝነት ይሠራል ነው ያሉት።
ኢዜአ ከዜና ባለፈ የሕብረ ብሔራዊ አንድነታችን ማፅኛ፣ አፍሪካውያን በራሳቸው አስተሳሰብ የራሳቸውን ታሪክ እንዲናገሩ ዋነኛ የትርክት ማሰራጫ መሰረተ ልማት ሆኖ እንዲቀጥልም አሳስበዋል፡፡
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ኢዜአ ለጀመረው የለውጥ ሥራ በትጋት ለሰሩ እና ለተባበሩ አካላትም ምስጋና አቅርበዋል፡፡