የሀገር ውስጥ ዜና

የጽ/ቤቱን ቼክ በማውጣት ከ17 ሚሊየን ብር በላይ በመመዝበር የተጠረጠሩ ግለሰቦች ላይ ክስ ተመሰረተ

By Adimasu Aragawu

August 05, 2025

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 29፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በህገወጥ መንገድ የጉለሌ ክ/ከተማ መሬት ልማትና አስተዳዳር ጽ/ቤትን ቼክ በማውጣት ከ17 ሚሊየን ብር በላይ በመመዝበር በሙስና ወንጀል የተጠረጠሩ ግለሰቦች ክስ ተመሰረተባቸው።

በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 1ኛ የሙስና ጉዳዮች ወንጀል ችሎት ክስ የተመሰረተባቸው ግለሰቦች 1ኛ በጉለሌ ክ/ከተማ መሬት ልማትና አስተዳዳር ጽ/ቤት የፋይናንስ ዳይሬክተር ዮሐንስ ወልዴ፣ 2ኛ የራይድ አሽከርካሪ ቴዎድሮስ ታደሰ፣ 3ኛ በግል ስራ የሚተዳደረው አብይ ታፈሰ በቅጽል ስሙ (ሃብታሙ ማሞ)፣ 4ኛ የጉለሌ ክ/ከተማ ፋይናንስ ቡድን መሪ ሃና ጌታቸው፣ 5ኛ የጉለሌ ክ/ከተማ ፋይናንስ ሲኒየር ባለሙያ ሰናይት አበበ፣ 6ኛ የጉለሌ ክ/ከተማ መሬት ልማትና አስተዳዳር ጽ/ቤት ኃላፊ ሰመሃር ንጉሴን ጨምሮ አጠቃላይ 19 ናቸው።

የፍትህ ሚኒስቴር የሙስና ወንጀል ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዐቃቤ ሕግ በተከሳሾቹ ላይ በየደረጃው ከባድ የሙስና ወንጀል ክስ አቅርቦባቸዋል።

በክሱ ዝርዝር ላይ እንደተመላከተው፤ የአዲስ አበበ ከተማ አስተዳዳር ገንዘብ መመሪያ ቁጥር 5/2003 በመተላለፍ በታሕሣሥ 15 ቀን 2017 ዓ.ም 1ኛ ተከሳሽ በጉለሌ ክ/ከ መሬት ልማትና አስተዳዳር ጽ/ቤት ፋይናንስ አስተዳዳር ዳይሬክተር ሆኖ ሲሰራ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሸገር ቅርንጫፍ የሂሳብ ቁጥሩ የተጠቀሰ ቼክ ፈርሞ ከባንክ ባለሙያ የተረከበ በኋላ ወደ መስሪያ ቤቱ እቃ መጋዘን በሞዴል 19 ገቢ ማድረግ ሲገባው ገቢ ሳያደርግ አንድ ቅጠል ቼክ ቆርጦ በማስቀረት የቼክ ፓዶችን ለ5ኛ ተከሳሽ ያስረከበ እና ቆርጦ ያስቀረውን ነጠላ የቼክ ቁጥር CD 47712615 የሆነውን ለ2ኛ ተከሳሽ በህገ ወጥ መልኩ ገንዘብ ወጪ እንዲያደርግበት አስተላልፏል።

2ኛ ተከሳሽ ከ1ኛ ተከሳሽ ገንዘብ በህገ ወጥ መልኩ ወጪ እንዲያደርግበት የተሰጠውን ቼክ በመጠቀም 7ኛ ተከሳሽን ‘የሚሰራ ስራ አለ የንግድ ፍቃድ ያለው ግለሰብ ካለ አገናኘኝ እና በፐርሰንት እንከፍላችዋለን’ በሚል ያግባባው እና 7ኛ ተከሳሽም የመሬት ካሳ ገንዘብ የሚከፈል እንደሆነ በማስመሰል 3ኛ ተከሳሽ ከመቐለ እንዲመጣ በ2ኛ ተከሳሽ ስልክ አግባብተው በማስመጣት ሃብታሙ ማሞ ለማ በሚል በሃሰት የተዘጋጀ የነዋሪነት መታወቂያ ከአቃቂ ቃሊቲ ክ/ከተማ ወረዳ 4 እንደተሰጠው ተመሳስሎ የተሰራ መታወቂያ ማቅረቡ ተመላክቷል።

በዚህ መልኩ በህገወጥ መንገድ የተገኘውን የቼክ ቅጠል በ3ኛ ተከሳሽ ሃሰተኛ ስም በማዘጋጀት፤ የጉለሌ ክ/ከተማ መሬት ልማትና አስተዳዳር ጽ/ቤት ሃላፊ 6ኛ ተከሳሽ እና 4ኛ ተከሳሽ ቡድን መሪን ፊርማ አስመስለው መፈረማቸው በክሱ ዝርዝር ተገልጿል።

ተከሳሾች የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳዳር የመሬት ልማትና አስተዳዳር ቢሮ ጉለሌ ቅ/ጽ/ቤት ስም በተከፈተው ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሸገር ቅርንጫፍ ተንቀሳቃሽ ሂሳብ ላይ በህገ ወጥ መንገድ የወጣን ቼክ በመመንዘር 17 ሚሊየን 849 ሺህ 621 ብር ከ47 ሳንቲም ወደ 3ኛ ተከሳሽ ሂሳብ እንዲገባ በማድረግ እና ገንዘቡን ወደ ተለያዩ ሰዎች ሂሳብ ተላልፎ ወጪ በመሆኑ እና ህገ ወጥ በሆነ መንገድ የተዘጋጀውን ቼክ መሰረት በማድረግ ክፍያ የተፈፀመ ስለሆነ፤ ለራሳቸው ጥቅም በማግኘት በዚሁ ልክ በመንግስት ጥቅም ላይ ጉዳት እንዲደርስ ማድረጋቸውን ጠቅሶ ዐቃቤ ሕግ በክሱ ዝርዝር ላይ አስፍሯል።

ዐቃቤ ሕግ በተከሳሾቹ ላይ የተሳትፎ ደረጃቸውን ጠቅሶ በ1996 ዓ.ም የወጣውን የወንጀል ህግ አንቀጽ 32 ንዑስ ቁጥር (1) ሀ፣ ለ እና አንቀጽ 36 እንዲሁም የሙስና ወንጀሎችን ለመደንገግ የወጣውን አዋጅ ቁጥር 881/2007 አንቀፅ 9(1) (ሀ) እና (2) አንቀጽ 13 ንዑስ ቁጥር (1) ሐ እና ንዑስ ቁጥር (2)፣ አንቀጽ 23(1) (ሀ) (ሐ)፣ ንዑስ ቁጥር 2 (ሀ) እና ንዑስ ቁጥር 3 እንዲሁም በወንጀል ድርጊት የተገኘ ገንዘብ ወይም ንብረት ህጋዊ አስመስሎ ማቅረብና ሽብርተኝነትን በገንዘብ መርዳትን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር የወጣውን አዋጅ ቁጥር 780/2005 አንቀፅ 29(1)(ሀ) እና ለ ስር የተደነገገውን ድንጋጌ መተላላፍ በሚል ያቀረበባቸው ክስ ዝርዝር ተከሳሾች ችሎት ቀርበው እንዲደርሳቸው ተደርጓል።

በታሪክ አዱኛ

ፈጣን እና ወቅታዊ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

YouTube www.youtube.com/@fanamediacorporation Facebook www.facebook.com/fanabroadcasting Telegram t.me/fanatelevision Website www.fanamc.com TikTok www.tiktok.com/@fana_television WhatsApp www.whatsapp.com/channel/0029VbB0dRxG8l59MUkoWR29 Amharic Entertainment YouTube www.youtube.com/@fanaentertainment Facebook www.facebook.com/wmccwaltamediaandcommunicationcorporate TikTok www.tiktok.com/@fanamc_entertainment Amharic Documentary YouTube www.youtube.com/@fanamcdocumentary በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡ ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስለሆኑ እናመሰግናለን!