አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 29፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በበጎ ፈቃድ አገልግሎታችን ቤተሰብ አፍርተናል አሉ የብሔራዊ በጎ ፈቃድ ማኅበረሰብ አገልግሎት ተሳታፊዎች።
የብሔራዊ በጎ ፈቃድ ማኅበረሰብ አገልግሎት መርሐ ግብር አስተባባሪ አለማየሁ ለማ ከፋና ፖድካስት ጋር በነበራቸው ቆይታ የመርሐ ግብሩ ዓላማ ወጣቶች ባላቸው ልምድ፣ እውቀት እና ጉልበት ማኅበረሰቡን እንዲያገለግሉ ማስቻል መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በጎ ፈቃደኞች ተመልምለው በስብዕና ግንባታ፣ ተወዳዳሪ ዜጋን በመፍጠር፣ በሀገር ግንባታና መሰል ጉዳዮች ላይ ስልጠና በመውሰድ ከመጡበት ክልል ውጭ ተሰማርተው የበጎ ፈቃድ አገልግሎት እንዲሰጡ ይደረጋልም ነው ያሉት።
በዚህም በጎ ፈቃደኞች የተሰማሩበትን ማኅበረሰብ ባህል ከማወቅና ቋንቋ ከመልመድ አልፈው በተመደቡባቸው አካባቢዎች ቤተሰብ መስርተው እየኖሩም ነው ብለዋል፡፡
የብሔራዊ በጎ ፈቃድ ማኅበረሰብ አገልግሎት መርሐ ግብር ተሳታፊዋ ጋዲሴ ዋቁማ በበኩሏ፥ በበጎ ፈቃድ አገልግሎት በተዘዋወረችባቸው ቦታዎች የማኅበረሰቡ አቀባበልና ፍቅር የተለየ መሆኑን አንስታለች።
ወገኖችን ማገዝ ከሚሰጠው ደስታ በላይ ከተሰማራንበት አካባቢ ነዋሪዎች ጋር የቅርብ ቤተሰባዊ ግንኙነት መመስረት በመቻላችን አሁንም ድረስ በበበጎ ፍቃድ አገልግሎት ቆይታ ከተዋወቅኳቸው ሰዎች ጋር እንጠያየቃለን ብላለች፡፡
መርሐ ግብሩ ባላት አቅም ሀገሯን እንድታግዝና ሰዎችን መርዳት እንድትችል ከፈጠረላት እድል ባሻገር ሁለተኛ ቤተሰብ ያገኘሁበትም ነው በማለት ተናግራለች።
የብሔራዊ በጎ ፈቃድ ማኅበረሰብ አገልግሎት መርሐ ግብር በዜጎች መካከል ማኅበራዊ ትስስር እንዲጎልብት፣ ሀገራዊ አንድነትና አብሮነት እንዲጠናከር ለማድረግና ሀገራቸውን እንዲያውቁ ሰፊ ዕድል የሚፈጥር ነው።
በብርሃኑ አበራ