አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 30፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ጾመ ፍልሰታን ስለሀገር ሰላም በመጸለይ እና ችግር ውስጥ የሚገኙ ወገኖችን በመርዳት ልናሳልፍ ይገባል አሉ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ፡፡
ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ የ2017 ዓ.ም የቅድስት ድንግል ማርያም ጾመ ፍልሰታን አስመልክተው የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
በመልዕክታቸውም እኛ በየጊዜው ጾምን እንድንጾም ያስፈለገበት ዋናው ምክንያት ፈቃደ ሥጋችንን በመግራት ለእግዚአብሔር ታዛዦች እንድንሆን ነው ብለዋል፡፡
ጾም የኃጢኣት መግቻ መሳሪያ በመሆኑ ሰውነታችንን ለግብረ ኃጢኣት ከሚያጋግሉ ምግቦች አርቀን በሰከነ መንፈስ እግዚአብሔርን እያሰብን ኃጢኣታችንንም እያስታወስን በንስሓ ወደ እርሱ ለመቅረብና ለሱ ለመታዘዝ እንጾማለን ነው ያሉት፡፡
እግዚአብሔር ከመሥዋዕት ይልቅ መታዘዝን ይወዳልና በጾምና በጸሎት ለሱ ልንታዘዝ ይገባል፤እግዚአብሔር በቅድስት ድንግል ማርያም ማሕፀን ሊያድር የቻለው ‹‹እንዳልኸኝ ይሁንልኝ›› ብላ ታዛዥነትዋን በገለጸች ጊዜ ነው፤ እኛም እንዳልከን ይሁንልን እያልን እንደ እርሷ ታዛዥ መሆን አለብን ሲሉም ተናግረዋል፡፡
ዛሬ በዓለማችን ያለው መተረማመስ ለእግዚአብሔር ያለመታዘዝ ያመጣው ጣጣ እንደሆነ ማንም አይስተውም፤ መታዘዙ ቢኖር ኖሮ የሰው ልጅ ሰውን የሚያድን ብቻ እንጂ ሰውን የሚገድል መሳሪያ አያመርትም ነበር ብለዋል ብፁዕነታቸው በመልዕክታቸው፡፡
ከዚህ አንጻር ዛሬም ለሰው ልጆች ሁሉ የምናስተላልፈው መልዕክት ‹‹በፍቅር ከሆነ ትንሹም ለሁሉ ይበቃልና ያለውን በጋራ በመጠቀም በፍቅርና በሰላም እንኑር›› የሚል ነው ሲሉ አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡
በጾመ ማርያም ሱባዔ ስለሀገር ሰላምና ስለሕዝብ ደኅንነት በመጸለይ፣ በልዩ ልዩ ምክንያት ችግር ውስጥ የሚገኙ ወገኖችን በመርዳት ልናሳልፍ ይገባል ሲሉ ማስገንዘባቸውንም ቤተክርስቲያኗ ለፋና ዲጂታል የላከችው መረጃ ያመላክታል፡፡
ፈጣን እና ወቅታዊ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
YouTube www.youtube.com/@fanamediacorporation Facebook www.facebook.com/fanabroadcasting Telegram t.me/fanatelevision Website www.fanamc.com TikTok www.tiktok.com/@fana_television WhatsApp www.whatsapp.com/channel/0029VbB0dRxG8l59MUkoWR29 Amharic Entertainment YouTube www.youtube.com/@fanaentertainment Facebook www.facebook.com/wmccwaltamediaandcommunicationcorporate TikTok www.tiktok.com/@fanamc_entertainment Amharic Documentary YouTube www.youtube.com/@fanamcdocumentary በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡ ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስለሆኑ እናመሰግናለን!