አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 1፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የደቡብ ኮሪያ ሪፐብሊክ መንግስት ዩኒሴፍ ኢትዮጵያ ሰብዓዊ ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው ዜጎች ለሚሰራው ስራ የ10 ሚሊየን ዶላር ድጋፍ አድርጓል።
የዩኒሴፍ ኢትዮጵያ ተወካይ አቡበከር ካምፖ (ዶ/ር) በዚሁ ወቅት÷ ድጋፉ ተቋሙ ለሚያከናውናቸው በጎ ተግባራት ፈጣን የፋይናንስ ድጋፍ አብዝቶ በሚሻበትና ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ምንጮች እየደረቁ ባለበት ወቅት የተደረገ እንደሆነ ተናግረዋል።
ድጋፉ የዩኒሴፍን ስራዎች ይበልጥ ውጤታማ እንደሚያደርግም ጠቁመዋል።
በኢትዮጵያ የደቡብ ኮሪያ ሪፐብሊክ አምባሳደር ጁንግ ካንግ ድጋፉ ለሰብዓዊ ፍላጎቶች መሳካት ያለንን ቁርጠኝነት ያሳየንበት ነው ብለዋል።
ኢትዮጵያና ደቡብ ኮሪያ በታሪካዊ ትስስር እና መከባበር ላይ የተመሰረተ የረጅም ጊዜ ወዳጅነት ያላቸው ሀገራት መሆናቸውን አንስተው÷ የደቡብ ኮሪያ ሕዝብ የኢትዮጵያ ሕዝቦች በኮሪያ ጦርነት ወቅት ያደረጉለትን አስተዋጽዖ ፈጽሞ አይረሳም ነው ያሉት።
መንግስታቸው በኢትዮጵያ ተጋላጭ በሆኑ አካባቢዎች ለህጻናትና ሴቶች ድጋፍ ማድረጉን ይቀጥላልም ብለዋል።
ድጋፉ በአፋር፣ አማራ፣ ኦሮሚያ፣ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ እና ትግራይ ክልሎች የሚገኙ 365 ሺህ ዜጎችን ተጠቃሚ እንደሚያደርግ ተገልጿል።
በዋናነት ግጭት በሚስተዋልባቸውና የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖ ጉዳት ባስከተለባቸው የተመረጡ አካባቢዎች የንጹህ መጠጥ ውሃ ተደራሽነት ለማሳደግ፣ የመጀመሪያ ደረጃ የጤና አገልግሎት ለማጠናከር፣ ፈጣን የህይወት አድን ስራዎችን ለማከናወንና ሰብዓዊ ድጋፎችን ተደራሽ ለማድረግ ይውላል።
የጤና፣ ውሃና ኢነርጂ እንዲሁም የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴሮች በተወካዮቻቸው በኩል የደቡብ ኮሪያ መንግስት ላደረገው ድጋፍ እውቅና ሰጥተው÷ ለፕሮግራሙ መሳካት የሚጠበቅባቸውን ኃላፊነት እንደሚወጡ አረጋግጠዋል።
በመራኦል ከድር
ፈጣን እና ወቅታዊ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
YouTube www.youtube.com/@fanamediacorporation Facebook www.facebook.com/fanabroadcasting Telegram t.me/fanatelevision Website www.fanamc.com TikTok www.tiktok.com/@fana_television WhatsApp www.whatsapp.com/channel/0029VbB0dRxG8l59MUkoWR29 Amharic Entertainment YouTube www.youtube.com/@fanaentertainment Facebook www.facebook.com/wmccwaltamediaandcommunicationcorporate TikTok www.tiktok.com/@fanamc_entertainment Amharic Documentary YouTube www.youtube.com/@fanamcdocumentary በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡ ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስለሆኑ እናመሰግናለን!