አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 1፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ዮሴፍ ቦጋለ ይባላሉ። የሶረን ትሬዲንግ ፒኤልሲ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ናቸው። በንግድ፣ በትራንስፖርት እና ሎጀስቲክስ፣ በሆቴል አገልግሎት እና በሌሎችም ዘርፎች ይሳተፋሉ።
እንደ እሳቸው ገለጻ የሚተነፈሰው ቢዝነስ፤ የሚወራው ገንዘብ በሆነባት የቻይናዋ ጓንጆ ከተማ ከከተሙ 15 ዓመታት ተቆጥረዋል። ጓንጆ የኢትዮጵያዊያን ነጋዴዎች መናኸሪያ ናት።
ከቻይናዎች ጋር ቢዝነስ ለመስራት ታማኝነት እና ሰዓት አክባሪነት አስፈላጊ መሆኑን የሚያነሱት አቶ ዮሴፍ÷ ኢትዮጵያዊያን በተለይ የስራን ክብር፣ እንዴት ተጋግዞ ቢዝነስ እንደሚሰራ፣ ራስን በራስ ማሳደግ እና የስራ ባህልን ከቻይናዎች ልንማር ይገባል ይላሉ።
ሶረን ትሬዲንግ ፒኤልሲ በቻይና የትራንስፖርት እና ሎጀስቲክስ አገልግሎት የሚሰጥ ድርጅት ነው። ከኢትዮጵያ እና ከሌሎች ሀገራት ወደ ቻይና ለሚያቀኑ ነጋዴዎች የሚፈልጉትን እቃ ያቀርባል።
ገዥዎች የሚፈልጓቸውን እቃ መገኛ መጠቆም፣ ስምምነት እና ግዥ መፈጸም፣ የመጋዘን አገልግሎት፣ ከቻይና ወደሚፈለገው ሀገራት ማጓጓዝ እና ሌሎችንም አገልግሎቶች ይሰጣል።
ልጅ እያሉ በንግዱ ዘርፍ የተሰማሩ አባታቸውን እና ታላላቅ ወንድሞቻቸውን እንደ አርዓያ በመውሰድ ወደ ንግዱ እንደተሳቡ ይናገራሉ።
እዚህ ለመድረሳቸው እና ለስኬታቸው ዋናው ሚስጥር ከቤተሰብ የተማርኩት እውቀት እና መረጃዎችን የማሰባሰብ ፍላጎቴ ነው ሲሉም ከፋና ፖድካስት ጋር በነበራቸው ቆይታ ተናግረዋል።
በልጅነታቸው አባታቸው ወደ ቻይና እየተመላለሱ የንግድ ሥራ ሲሰሩ እንደነበር የገለጹት አቶ ዮሴፍ÷ በዚህም ወደ ቻይና የማቅናትና የማየት ፍቅር እንዳደረባቸው ጠቁመዋል።
ከዚያም የዛሬ 15 ዓመት ገደማ ወደ ቻይና ጓንጆ ከተማ ለትምህርት በማቅናት ከትምህርታቸው ጎን ለጎን ያላቸውን ጊዜ በመጠቀም የንግድ ስራ መጀመራቸውን አስታውሰዋል።
ቻይና እንደገቡ ቋንቋን በፍጥነት መማር መቻላቸው ወደ ቻይና የሚያቀኑ ነጋዴዎችን በቋንቋ በማገዝ ወደ ንግዱ የሚገቡበትን እድል አስፍተዋል።
ኢትዮጵያዊያን እና ከሌሎችም ሀገራት የሚመጡ ነጋዴዎች እቃዎችን እንዴት እና የት አካባቢ እንደሚያገኙ የተሟላ መረጃ ለመስጠት እና ለማገናኘት በማሰብ መፍትሔ ላይ የሚሰራ ድርጅት አቋቋሙ። ይህ ድርጅትም አሁን በትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ዘርፍ መፍትሔ ይዞ በመምጣት በርካታ ስራዎችን እንደሰራ አንስተዋል።
በኢትዮጵያ ውስጥ ደግሞ በማኑፋክቸሪንግ፣ የኢትዮጵያን ቡና ለቻይና ገበያ በማቅረብ እና በሌሎችም ዘርፎች ኢንቨስት እያደረገ ይገኛል ብለዋል።
በሁሉም ሀገራት የሚንቀሳቀስ ዓለም አቀፍ አገልግሎት ሰጭ የሆኑ በርካታ ተወዳዳሪ ድርጅቶች እንዳሉበት የሚገልጹት አቶ ዮስፍ÷ ተፎካካሪዎቻችንን በመቀራረብ እና አብረን መስራት በምንችልባቸው ጉዳዮች ላይ በመምከር እንዲሁም የተሻለ የጋራ ገበያ በመፍጠር የቢዝነስ አጋራችን እናደርጋቸዋለን ይላሉ።
በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ውስጥ አዳዲስ የኢኮኖሚ ሪፎርም መኖሩ ተስፋ ሰጭ መሆኑንም አንስተዋል።
የሶረን ትሬዲንግ ፒኤልሲ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ዮሴፍ ቦጋለ ከፋና ፖድካስት ጋር የነበራቸውን ቆይታ ለመከታተል ማስፈንጠሪያውን ይጫኑ👇https://youtu.be/4YiMN95Z3IA?si=EPJGOOqrVnuegLj9
በብርሃኑ አበራ
ፈጣን እና ወቅታዊ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
YouTube www.youtube.com/@fanamediacorporation Facebook www.facebook.com/fanabroadcasting Telegram t.me/fanatelevision Website www.fanamc.com TikTok www.tiktok.com/@fana_television WhatsApp www.whatsapp.com/channel/0029VbB0dRxG8l59MUkoWR29 Amharic Entertainment YouTube www.youtube.com/@fanaentertainment Facebook www.facebook.com/wmccwaltamediaandcommunicationcorporate TikTok www.tiktok.com/@fanamc_entertainment Amharic Documentary YouTube www.youtube.com/@fanamcdocumentary በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡ ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስለሆኑ እናመሰግናለን!