አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 1፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ጤና ሚኒስቴር የኤች አይ ቪ/ኤድስ ስርጭትን ለመከላከል የሚያስችሉ ስራዎች እየተሰሩ ናቸው አለ።
በሚኒስቴሩ የኤች አይ ቪ/ኤድስ መከላከል እና መቆጣጠር መሪ ስራ አስፈፃሚ ፍቃዱ ያደታ እንዳሉት÷ በተለያዩ መንገዶች የተከናወኑ የቫይረሱን ስርጭት የመከላከል ስራዎች ውጤት ማስመዝገብ ችለዋል።
አሁን ላይ እንደ ሀገር የቫይረሱን ስርጭት ለመከላከል የሚያስችሉ ስራዎች እየተሰሩ መሆናቸውን ጠቅሰው÷ የባህርይ ለውጥ ሊመጣ ባለመቻሉ የተፈጠሩ መዘናጋቶች ግን እንቅፋት እንደሆኑ ለፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን ተናግረዋል።
ይሁን እንጂ አሁንም በተለያዩ አካባቢዎች ያለው የስርጭት መጠን ትኩረት የሚሻ መሆኑን አንስተው÷ በየዓመቱ ከ7 ሺህ በላይ አዳዲስ ሰዎች በቫይረሱ እንደሚያዙ ነው ያመላከቱት።
በዚህም ዕድሜያቸው ከ24 ዓመት በታች የሆኑ ወጣቶች በከፍተኛ ቁጥር ተጋላጭ እየሆኑ መምጣታቸውን ጠቁመዋል።
አዲስ አበባ ከተማን ጨምሮ ጋምቤላ፣ አማራ እና ትግራይ ክልሎች ከፍተኛ ስርጭት የሚስተዋልባቸው እንደሆኑ ገልጸው÷ በሶማሌ ክልል ያለው የቫይረሱ ስርጭት ደግሞ ዝቅተኛ መሆኑን ነው የተናገሩት።
በሰለሞን ይታየው