የሀገር ውስጥ ዜና

አረንጓዴ ዐሻራን በሥርዓተ ትምህርት ማስደገፍ…

By Yonas Getnet

August 07, 2025

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 1፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) አረንጓዴ ዐሻራን በሥርዓተ ትምህርት በማስደገፍ ችግኝ የመትከል እሴትን በተማሪዎች ዘንድ ማስረጽ ይገባል አሉ ምሁራን።

በጅማ ዩኒቨርሲቲ የግብርና እና እንስሳት ህክምና ኮሌጅ የሥነ ምህዳር መምህርና ተመራማሪ ጥበቡ አለሙ (ዶ/ር) ትምህርት ቤቶች በንድፈ ሀሳብ ደረጃ ችግኝ መትከልን ቢያስተምሩም በተግባር የተደገፈ አለመሆኑን ጠቁመዋል።

ከዚህ ቀደም ዛፍ በመትከል አካባቢን አረንጓዴ በማልበስ ረገድ ትምህርት ቤቶች እና ተማሪዎች የነቃ ተሳትፎ ያደርጉ እንደነበረ አስታውሰው÷ አሁንም ይህ ተግባር ሊጠናከር ይገባል ብለዋል።

በዩኒቨርሲቲው የትምህርት እና ሥነ ባህሪ ኮሌጅ የሥርዓተ ትምህርት መምህርና ተመራማሪ አቢ ለማ (ዶ/ር) በበኩላቸው÷ ተማሪዎች በአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር ላይ የነቃ ተሳትፎ ማድረግ እንዳለባቸው ተናግረዋል።

ትውልድ የሚቀረጽባቸውን የተራቆቱ ትምህርት ቤቶች ላይ ተማሪዎች ችግኝ የመትከል እና የመንከባከብ ባህል እንዲያሳድጉ የመምህራን ሚና የላቀ መሆኑንም ጠቁመዋል።

የተማሪዎችን ክህሎት ከግብርና ጋር በማዛመድ ችግኝ የመትከል ባህል አብሯችው እንዲያድግ መስራት ይገባል ያሉት ደግሞ በጅማ ዩኒቨርሲቲ የትምህርት እቅድ አስተዳደር መምህር አንዷለም ሞላ ናቸው።

በወርቅአፈራው ያለው