የሀገር ውስጥ ዜና

ኢትዮጵያ የባሕር በር ለማግኘት የምታደርገውን ጥረት እደግፋለሁ – ቱርክሜኒስታን

By Hailemaryam Tegegn

August 11, 2025

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 5፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ቱርክሜኒስታን ፥ ኢትዮጵያ የባሕር በር ለማግኘት የምታደርገውን ጥረት እደግፋለሁ አለች፡፡

በፓኪስታን ተቀማጭነታቸውን በማድረግ በቱርከሜኒስታን የኢትዮጵያ አምባሳደር ጀማል በከር (ዶ/ር) ከሀገሪቱ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ራሺድ ሜሬዶቭ ጋር ተወያይተዋል።

አምባሳደር ጀማል (ዶ/ር) በዚህ ወቅት እንዳሉት ÷ ኢትዮጵያ ውስብስብ በሆኑ የውስጥና የውጭ ሴራዎች ምክንያት ያጣችውን ታሪካዊና ተፈጥሯዊ የባሕር በር ባለቤትነት በድጋሚ ለማግኘት እየሠራች ነው፡፡

ኢትዮጵያ የባሕር በር ለማግኘት የምታደርገው ጥረት ከሀገራዊ ጥቅም ባለፈ ለቀጣናዊ ውህደት፣ ልማትና ደህንነት ወሳኝ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

የባሕር በር ጥያቄውን በሰላማዊና ዲፕሎማሲያዊ መንገድ የዓለም አቀፍ ሕጎችን መሰረት በማድረግ ለማስከበር ቁርጠኛ መሆኗንም ነው ያብራሩት፡፡

ኢትዮጵያ በዓለም በሕዝብ ብዛት ትልቋ የባሕር በር የሌላት ሀገር መሆኗን ያነሱት አምባሳደሩ ፥ የጂኦግራፊ እስረኛ ሆና መቆየት እንደሌለባት አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡

ራሺድ ሜሬዶቭ በበኩላቸው÷ ቱርክሜኒስታን የኢትዮጵያን የባሕር በር ጥያቄ እንደምትጋራና እንደምትደግፍ አረጋግጠዋል።

ቱርክሜኒስታን በቀጣናዊ ትብብር አስፈላጊነት እና እያንዳንዱ ሀገር የባሕር በር የማግኘት መሰረታዊ መብት እንዳለው እንደምታምን አመልክተዋል፡፡

የባሕር በር በሌላቸው ሀገራት መካከል ትብብርና ዓለም አቀፍ ድጋፍ እንደሚያስፈልግም ነው ያስገነዘቡት፡፡

ሁለቱም ወገኖች በዓለም አቀፍ መድረኮች ላይ ለመተባበርና የሁለትዮሽ ግንኙነታቸውን ለማጠናከር መስማማታቸውንም ኤምባሲው ለፋና ዲጂታል የላከው መረጃ አመልክቷል፡፡