የሀገር ውስጥ ዜና

በቢሾፍቱ አቅራቢያ ለሚገነባው አውሮፕላን ማረፊያ የፋይናንስ እንቅስቃሴዎች ውክልና ሰነድ ተፈረመ

By Yonas Getnet

August 11, 2025

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 5፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ አየር መንገድ እና የአፍሪካ ልማት ባንክ በቢሾፍቱ አቅራቢያ ለሚገነባው አዲስ አውሮፕላን ማረፊያ ፕሮጀክት የፋይናንስ እንቅስቃሴዎች አመቻቺነት የውክልና ሰነድ ተፈራርመዋል።

በፊርማ ሥነ ሥርዓቱ የገንዘብ ሚኒስትር አሕመድ ሺዴ፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ቦርድ ሊቀመንበር ሌ/ጄ ይልማ መርዳሳ እና የአፍሪካ ልማት ባንክ ፕሬዚዳንት አኪንውሚ አዴሲና ተገኝተዋል፡፡

በስምምነቱ መሰረት የአፍሪካ ልማት ባንክ የአዲሱን አውሮፕላን ማረፊያ ፕሮጀክት የፋይናንስ ሥራዎች በውክልና ተረክቦ የሚሰራ ይሆናል፡፡

አዲሱ የአውሮፕላን ማረፊያ አራት ማኮብኮቢያዎች፣ ዘመኑን የዋጁ የመንገደኞች እና የጭነት መገልገያዎችን እንደሚያካትት ተመላክቷል፡፡

በአምስት ምዕራፎች የሚከናወነው የፕሮጀክቱ ግንባታ ሲጠናቀቅ በዓመት ከ100 ሚሊየን በላይ መንገደኞችን ማስተናገድ ያስችላል፡፡

ፕሮጀክቱ የአቪዬሽን ዘርፉንና ሀገራዊ የምጣኔ ሃብት ዕድገትን በማበረታታት ለሥራ እድል ፈጠራ እንዲሁም ለቀጣናዊ ንግድና ቱሪዝም መነቃቃት ከፍተኛ ሚና እንደሚጫዎት ይጠበቃል፡፡

በ3 ሺህ 975 ሔክታር መሬት ላይ የሚገነባው ፕሮጀክቱ ሲጠናቀቅ አሁን ያለውን የኢትዮጵያ አቪዬሺን አቅም በአራት እጥፍ ያሳድጋል፡፡

አኪንውሚ አዴሲና በዚሁ ወቅት እንዳሉት÷ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እና መንግስታቸው ለባንኩ ላደረጉት ትብብርና ቁርጠኝነት አመስግነዋል፡፡

የተለያዩ አፍሪካ ሀገራት ተወካዮች በበኩላቸው÷ አየር መንገዱ የአህጉሪቱ የአቪዬሽን ዘርፍ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ ሆኖ እንዲዘልቅ ከማስቻሉ ባለፈ የፓን አፍሪካ ምልክት እንደሆነ ተናግረዋል።

በመሳፍንት ብርሌ