አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 6፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የቻይና ፕሬዚዳንት ሺ ጂንፒንግ ታዳጊ የደቡባዊ ሀገራት ዓለም አቀፋዊ ፍትሃዊነትን በማስፈን ጥቅማቸውን ለማስከበር በትብብር እንዲሰሩ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ፕሬዚዳንት ሺ ከብራዚሉ አቻቸው ሉላ ዳ ሲልቫ ጋር የሀገራቱን ሁለትዮሽ ግንኙነትና ትብብር በተመለከተ ባደረጉት ውይይት÷ ቻይና እና ብራዚል ጠንካራ የጋራ ታሪክና እድገት ራዕይ ያላቸው ሀገራት መሆናቸውን አንስተዋል፡፡
ቻይና ከብራዚል ጋር ያሏትን የልማት እድሎች ለመጠቀም እና በጋራ ተጠቃሚነት መርህ ላይ የተመሰረተውን የሁለትዮሽ ትብብር ለማጠናከር ቁርጠኛ መሆኗን አስገንዝበዋል፡፡
በታሪክ ብራዚላውያን ሉዓላዊነታቸውን እና ነፃነታቸውን እንዲጠብቁ ቻይና ድጋፍ ማድረጓን ያወሱት ፕሬዚዳንቱ÷ ሁሉም ሀገራት ባለብዙ ወገን የዓለም ስርዓት እንዲፈጠር እና የሀገራት የኢኮኖሚና ፖለቲካ ነፃነት እንዲከበር መተባበር አለባቸው ብለዋል፡፡
ብሪክስ+ በሀገራት ላይ የሚደረገውን ጫና በመከላከል ባለብዙ ወገን የዓለም ስርዓት እንዲፈጠር አስተዋፅኦ እያደረገ መሆኑን አመልክተዋል።
የታዳጊ ደቡባዊ ሀገራት ዓለም አቀፋዊ ፍትሃዊነት እንዲሰፈን፣ የዓለም አቀፍ ግንኙነት ህጎችን ለማስከበር እና የታዳጊ ሀገራትን ህጋዊ መብትና ጥቅም ለማስጠበቅ በትብብር እንዲሰሩም ጥሪ አቅርበዋል፡፡
የብራዚሉ ፕሬዚዳንት ሉላ ዳ ሲልቫ በቡላቸው÷ ቻይና የባለብዙ ወገን ግንኙነትና እና ነፃ የንግድ መርሆዎችን ለማስጠበቅ እንዲሁም በዓለም አቀፋዊ ጉዳዮች ላይ ያላትን ቁርጠኝነት አድንቀዋል፡፡
ብራዚል በሀገራት ላይ የሚደረጉ አንድ ወገን ጫናዎችን በመከላከል የታዳጊ ሀገራትን ጥቅም ለማስከበር በቁርጠኝነት እንደምትሰራም አረጋግጠዋል፡፡
ብራዚል በብሪክስ+ እና በሁለቱ ሀገራት የሁለትዮሽ ግንኙነት ማዕቀፍ ከቻይና ጋር የምታደርገውን ግንኙነት እና ትብብር አጠናክራ ትቀጥላለች ማለታቸውን ሲጂቲኤን ዘግቧል፡፡
በሚኪያስ አየለ