አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 6፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ በዓለም አቀፍ ተቋማት ተሰሚነት እና ተቀባይነት እንዲያገኝ የጋራ ጥረት ማድረግ ያስፈልጋል፡፡
ብልፅግና ፓርቲ ሰሞኑን ባወጣው መግለጫ የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ አጀንዳ ሆኖ መቀጠሉን እና መንግስት በርካታ ስራዎችን እያከናወነ እንደሚገኝ አስታውቋል፡፡
በዚህ መነሻነት ፋና ዲጂታል ያነጋገራቸው የቀጣናዊ ሰላምና ፀጥታ መምህርና ተመራማሪው ቻን ዮም (ዶ/ር)፤ ኢትዮጵያ ያነሳችው የባህር በር ጥያቄ ምላሽ እንዲያገኝ የተደረገው ዲፕሎማሲያዊ ጥረት ይደነቃል ብለዋል።
የባህር በር ጥያቄው በዓለም አቀፍ ህግ መሰረት በጋራ ተጠቃሚነት መርህ መልስ እንዲያገኝ አበረታች ጥረት እየተደረገ እንደሆነ ተናግረዋል።
እንደ የምስራቅ አፍሪካ ልማት በይነ መንግስታት (ኢጋድ)፣ የምስራቅ አፍሪካ ማህበረሰብ፣ አፍሪካ ህብረት እና ሌሎች ቀጣናዊ፣ አህጉራዊ እና ዓለም አቀፍ ተቋማት የኢትዮጵያ ጥያቄ ምላሽ እንዲያገኝ የሚያስችል የጋራ ጥረት እንዲያደርጉ መሰራት እንዳለበት አስገንዝበዋል።
ጥያቄው ለመንግስት ብቻ የሚተው አይደለም ያሉት መምህርና ተመራማሪው÷ ምሁራን ጥያቄው የፍትሐዊ ተጠቃሚነት ጥያቄ መሆኑን የሚያስረዱ ጥናታዊ ፅሁፎች እንዲዘጋጁ እና የውይይት መድረኮች እንዲፈጠሩ ማድረግ አለባቸው ነው ያሉት።
በውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት የባለብዙ ወገን ጉዳዮች ተመራማሪ አዲስ አለማሁ በበኩላቸው÷ የዓባይ ወንዝን የተፋሰሱ ሀገራት በጋራ እንደሚጠቀሙበት ሁሉ የባህር ዳርቻ ያላቸው ሀገራትም በጋራ ተጠቃሚነት መርሕ አዎንታዊ ምላሽ መስጠት አለባቸው ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ ጥያቄ አዳጊ ኢኮኖሚዋን ማሳለጥ የሚችል የባህር በር ማግኘት እና ቀጣናዊ ደህንነትን ማረጋገጥ እንደሆነ ተናግረዋል።
ምስራቅ አፍሪካ ሀገራት በኢኮኖሚ፣ በማህበራዊ፣ በሰላምና ፀጥታ እንዲሁም በሌሎች ቀጣናዊ ትስስር ላይ በጋራ እየሰሩ እንደሚገኙ ጠቅሰው፤ የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ ምላሽ ማግኘት ትስስሩን ይበልጥ ያጠናክራል ነው ያሉት።
በሚኪያስ አየለ