ስፓርት

ለሸገር ከተማ እግር ኳስ ክለብ 36 ሚሊየን ብር የገንዘብ ሽልማት ተበረከተ

By Hailemaryam Tegegn

August 12, 2025

ለሸገር ከተማ እግር ኳስ ክለብ 36 ሚሊየን ብር የገንዘብ ሽልማት ተበረከተ

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 6፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በ2017 ዓ.ም በሁለቱም ፆታ ከከፍተኛ ሊግ ወደ ኢትዮጵያ ፕሪሚየር ማደግ የቻለው ሸገር ከተማ የዕውቅናና ሽልማት መርሐ ግብር አካሂዷል።

የሸገር ከተማ ከንቲባ ተሾመ አዱኛ (ዶ/ር) በዚሁ ወቅት ባደረጉት ንግግር፥ የሸገር ራዕይ ዘላቂ ድሎችን ማስመዝገብ የሚችል ክለብ ማቋቋም ነው ብለዋል፡፡

የከተማ ወጣቶችና ስፖርት ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ናስር ሁሴን በበኩላቸው፥ የእግር ኳስ ክለቡ በተመሰረተ በጥቂት ዓመታት ውስጥ ወደ ፕሪሚየር ሊግ ማደጉን ጠቅሰው፥ የከተማዋን አላማ ለማሳካት በትክክለኛው መስመር ላይ ነው፡፡

በተደረገው የዕውቅናና ሽልማት መርሐ ግብር ለሁለቱም ቡድን ማለትም ለሸገር ከተማ የሴቶችና ወንዶች ቡድን ተጨዋቾች በተሰለፉባቸው ደቂቃ ተሰልቶ የገንዘብ ሽልማት ተበርክቶላቸዋል፡፡

ለሁለቱም ቡድን ዋና አሰልጣኞች 500 ሺህ ብር እና ባለ 3 መኝታ መኖሪያ ቤት እንዲሁም ለምክትል አሰልጣኞች ደግሞ 250 ሺህ ብር እና ባለ 2 መኝታ መኖሪያ ቤት በስጦታ ተበርክቷል።

የሸገር ከተማ አስተዳደር ለክለቡ የበላይ አመራሮች ጨምሮ በአጠቃላይ 36 ሚሊየን ብር ሽልማት አበርክቷል፡፡

በደጀኑ ጎንፋ