አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 7፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በቻይና እና ህንድ መካከል ለአምስት ዓመት ተቋርጦ የቆየው የአውሮፕላን ቀጥታ በረራ ወደ ተለያዩ መዳረሻ ከተሞች ይጀምራል።
ውሳኔው በዓለማችን ብዙ ህዝብ ያላቸው ቻይና እና ህንድ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸው እና የኢኮኖሚ ትብብራቸው እያደገ መምጣቱን ተከትሎ የተደረሰ መሆኑ ተመላክቷል፡፡
በዚህ መሰረት የህንድ መንግስት ኤር ኢንዲያ እና ኢንዲጎ የተባሉት ግዙፍ ኩባንያዎች በቀጣዮቹ ሳምንታት ወደ ቻይና መዳረሻዎች በረራ እንዲጀምሩ ጠይቋል፡፡
በሀገራቱ መካከል ሲካሄድ የነበረው የአውሮፕላን ቀጥታ በረራ በፈረንጆቹ 2020 የተከሰተውን የኮቪድ 19 ወረርሽኝ ተከትሎ መቋረጡ ይታወሳል።
በረራውን ዳግም ለማስጀመር ባለፈው ዓመት በሩሲያ ካዛን በተካሄደው የብሪክስ ጉባኤ ወቅት የህንድ ጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ እና የቻይና ፕሬዚዳንት ሺ ጂንፒንግ መክረው ነበር።
ከሳምንት በፊት በቲያንጂን በተካሄደው የሻንጋይ ትብብር ጉባኤ ላይ መሪዎቹ የቀጥታ በረራውን ማስቀጠል ጨምሮ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ትብብራቸው እንዲጠናከር ከስምምነት ላይ ደርሰዋል፡፡
ኒው ዴልሂ ከወራት በፊት ለቻይና ዜጎች ስትሰጥ የነበረውን የቱሪስት ቪዛ ከአምስት ዓመት በኋላ እንደገና የጀመረች ሲሆን፤ ቤጂንግም በተመሳሳይ ከቻይና ወደ ህንድ በሚጓጓዘው የዩሪያ ምርት ጥላ የነበረውን ማዕቀብ አንስታለች፡፡
ፈጣን የኢኮኖሚ እድገት ያላቸው ህንድ እና ቻይና የበረራ አግልገሎትን ሳይጨመር በ2023 የነበራቸው የሁለትዮሽ የንግድ ልውውጥ 110 ቢሊየን ዶላር መድረሱን አቪየሽን ኤቱ ዜድ እና አርቲ ዘግበዋል፡፡
በሚኪያስ አየለ