የሀገር ውስጥ ዜና

የ400 ሜጋ ዋት ሶላር ፓርክና 700 ኪሎዋት ሰዓት ሶላር ሚኒ ግሪድ የማስጀመር ስምምነት

By sosina alemayehu

August 13, 2025

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 7፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ከዓለም አቀፉ ሶላር አሊያንስ ጋር የ400 ሜጋ ዋት ሶላር ፓርክ እና 700 ኪሎዋት ሰዓት ሶላር ሚኒ ግሪድ ለማስጀመር የሚያስችል ስምምነት ተፈራርሟል።

የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ዴኤታው ሱልጣን ወሊ (ዶ/ር) በዚህ ወቅት እንዳሉት÷ ኢትዮጵያ ከጸሃይ ኃይልን የማመንጨት ከፍተኛ አቅም ቢኖራትም እስካሁን ከዘርፉ የምታገኘው ኃይል ከ10 ሜጋ ዋት በታች ነው።

በሀገሪቱ ከዋናው መስመር ርቀውና ተበታትነው የሚገኙ መንደሮች ኃይልን ማግኘት የማይችሉ በመሆናቸው ለእነዚህ አካባቢዎች የታዳሽ ኃይልን ተደራሽ ለማድረግ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን አንስተው÷ የዛሬው ስምምነትም የዚህ አካል እንደሆነ ጠቁመዋል።

በኢትዮጵያ በሶላር ኃይል የሚሰራ ፓምፕን ተደራሽ በማድረግ ግብርናን ለማዘመን እንዲሁም የካርበን ልቀትን ዜሮ ያደረገ ኃይል በማስፋፋት የአየር ብክለት ለመከላከልም እየተሰራ መሆኑ ተገልጿል።

ኢትዮጵያን ጨምሮ 124 አባል ሀገራት ያሉት ዓለም አቀፉ ሶላር አሊያንስ÷ ባለፉት አራት ዓመታት የሶላር ቴክኖሎጂዎችን በኢትዮጵያ ለማስፋት እየሰራ መሆኑም ተመላክቷል።

በይስማው አደራው