ጤና

የወባ በሽታ ስርጭትን ለመከላከል 13 ሚሊየን የአልጋ አጎበር ይሰራጫል

By Adimasu Aragawu

August 16, 2025

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 10፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በዘንድሮው ዓመት የወባ በሽታ ስርጭትን ለመከላከል 13 ሚሊየን የአልጋ አጎበር ይሰራጫል አለ የጤና ሚኒስቴር።

በሚኒስቴሩ የበሽታዎች መከላከልና መቆጣጠር መሪ ስራ አስፈጻሚ ዶ/ር ህይወት ሰለሞን ለፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን እንዳሉት÷ 75 በመቶ የሚሆነው የሀገሪቱ ክፍል ለወባ በሽታ ስርጭት ምቹ ነው።

በዚህም ከክረምት ወቅት መጠናቀቅ በኋላ ከመስከረም እስከ ታሕሣሥ ወር መጨረሻ ባለው ጊዜ ከፍተኛ የወባ በሽታ ስርጭት ሊኖር እንደሚችል ጠቁመዋል።

ባለፉት ሁለት ዓመታት እስከ ጥር ድረስ የበሽታው ስርጭት ጨምሮ እንደነበር አስታውሰው÷ በተሰራው ከፍተኛ ርብርብ ከጥር ወር በኋላ ካለፉት ሁለት ዓመታት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር ስርጭቱ በተከታታይ ሳምንታት እየቀነሰ መምጣቱን አንስተዋል።

በሰሜን ምዕራብ፣ ደቡብ እና ምዕራብ የሀገሪቱ አካባቢዎች የበሽታው ስርጭት ከፍተኛ መሆኑን ገልጸው÷ የበሽታውን ስርጭት ለመከላከል በዘንድሮው ዓመት 13 ሚሊየን የአልጋ አጎበር ለማሰራጨት ታቅዷል ብለዋል።

በዚህም እስካሁን 2 ነጥብ 4 ሚሊየን አጎበር ለተጠቃሚዎች እንደቀረበና 3 ነጥብ 5 ሚሊየን የሚሆነው ደግሞ እየተሰራጨ መሆኑን አመልክተዋል።

በአጠቃላይ የመስከረም ወር ከመጠናቀቁ በፊት ወደ 6 ሚሊየን የአልጋ አጎበር ለማሰራጨት መታቀዱን የገለጹት ዶ/ር ህይወት÷ እስከ ታሕሣሥ ወር 7 ሚሊየን የአልጋ አጎበር የግዥ ሂደት እንደሚጠናቀቅ አብራርተዋል።

በተመሳሳይ ባለፈው ዓመት በ2 ሚሊየን ቤቶች ላይ የኬሚካል ርጭት መካሄዱንና ዘንድሮም ተጨማሪ አንድ ሚሊየን ቤቶች ላይ የኬሚካል ስርጭት እንደሚካሄድ ተናግረዋል።

በ19 ሚሊየን ዶላር ወጪ አስፈላጊው ግብዓት በበቂ ሁኔታ ሳይቆራረጥ እንዲደርስ እየተደረገ ነው ያሉት ዶ/ር ህይወት÷ በጤና ተቋማትም በቂ የሆነ የአገልግሎት ግብዓት ቀርቧል ብለዋል ።

ዘንድሮ ተጨማሪ 10 ሚሊየን የወባ ታማሚዎችን መመርመር የሚያስችል ግብዓት በማድረስ ወደ 25 ሚሊየን ሰዎች የወባ በሽጻን እንዲመረመሩ መደረጋቸውን ገልጸዋል።

ማህበረሰቡ የወባ በሽታን ለመከላከል ከጤና ባለሙያዎች የሚሰጡ ምክረ ሐሳቦችን በአግባቡ መተግበር እና የአልጋ አጎበርን በስርዓት እንዲጠቀምም መልዕክት አስተላልፈዋል።

በመሳፍንት እያዩ

ፈጣን እና ወቅታዊ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

YouTube www.youtube.com/@fanamediacorporation Facebook www.facebook.com/fanabroadcasting Telegram t.me/fanatelevision Website www.fanamc.com TikTok www.tiktok.com/@fana_television WhatsApp www.whatsapp.com/channel/0029VbB0dRxG8l59MUkoWR29 Amharic Entertainment YouTube www.youtube.com/@fanaentertainment Facebook www.facebook.com/wmccwaltamediaandcommunicationcorporate TikTok www.tiktok.com/@fanamc_entertainment Amharic Podcast YouTube www.youtube.com/@fanamcpodcast በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡ ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስለሆኑ እናመሰግናለን!