ቢዝነስ

የባሕር ዳር ልዩ ኢኮኖሚ ዞን ከ3 ነጥብ 4 ሚሊየን ዶላር በላይ ምርት ለውጭ ገበያ አቀረበ

By Abiy Getahun

August 16, 2025

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 10፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በተጠናቀቀው የ2017 በጀት ዓመት የባሕር ዳር ልዩ ኢኮኖሚ ዞን 3 ሚሊየን 400 ሺህ 647 ዶላር ዋጋ ያለው ምርት ለውጭ ገበያ አቅርቧል።

የልዩ ኢኮኖሚ ዞኑ ዋና ስራ አስኪያጅ ጥሩየ ቁሜ ለፋና ዲጂታል እንዳሉት÷ በበጀት ዓመቱ ለውጭ ገበያ ለማቅረብ የታቀደው 500 ሺህ የአሜሪካን ዶላር ገቢ ለማግኘት ነበር።

በልዩ ኢኮኖሚ ዞን የተኪ ምርቶች ላይ በትኩረት በመስራት ለሀገር ውስጥ ገበያ 4 ሚሊየን 934 ሺህ 127 የአሜሪካን ዶላር የሚያወጣ ምርት መቅረቡንም ተናግረዋል።

ይህም ትራንስፎርመር በማምረት፣ አኩሪ አተር ዘይት እንዲሁም ከቦቆሎ ስታርች በማምረትና ለሀገር ውስጥ ገበያ በማቅረብ የተገኘ መሆኑን ነው ያስረዱት።

የልዩ ኢኮኖሚ ዞኑ የገበያ ትስስርን በመፍጠር ረገድ የተሻለ ውጤት መመዝገቡን አንስተው÷ በፓርኩ ውስጥ ባሉ ድርጅቶችና የሀገር ውስጥ አምራቾች መካከል ያለውን ትስስር በማጠናከር የቴክኖሎጂ ሽግግር ማጠናከር ተችሏል ብለዋል።

በዚህም ከአምራቾች ጋር 3 ሚሊየን 938 ሺህ 127 የአሜሪካን ዶላር የገበያ ትስስር መፈጠሩን እንዲሁም 1 ሺህ 200 አርሶ አደሮችና 10 ማህበራት ጋር አኩሪ አተርና በቆሎ አምራቾች ጋር ትስስር መፈጠሩን ጠቁመዋል።

በተጨማሪም ለ205 አምራቾች የ12 ወራት የቴክኖሎጂ ስልጠና መሰጠቱን አመልክተዋል።

በልዩ ኢኮኖሚ ዞኑ ስምንት የማምረቻ ሼዶች መኖራቸውን ገልጸው÷ አምስቱ ለባለሃብቶች ተላልፈው የተለያዩ ምርቶችን እያመረቱ መሆናቸውን አስረድተዋል።

በተቋሙ ለዜጎች የስራ ዕድል በመፍጠር ረገድ ለ5 ሺህ 842 ዜጎች ጊዜያዊ እና ቋሚ የስራ ዕድል መፈጠሩን ወ/ሮ ጥሩየ ተናግረዋል።

በአረንጓዴ ልማት በተሰራው ስራም ከተቋሙ ሊወጣ የነበረውን 37 ሚሊየን ብር ወጪ በ6 ነጥብ 6 ሚሊየን ብር በማከናወን 31 ሚሊየን ብር በመቆጠብ ለተቋሙ ማስቀረት መቻሉንና በዚህም ግቢውን ውብና ፅዱ በማድረግ የባለሃብቱን የእርካታ ደረጃ ማሳደግ ተችሏል ብለዋል።

በአድማሱ አራጋው

ፈጣን እና ወቅታዊ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

YouTube www.youtube.com/@fanamediacorporation Facebook www.facebook.com/fanabroadcasting Telegram t.me/fanatelevision Website www.fanamc.com TikTok www.tiktok.com/@fana_television WhatsApp www.whatsapp.com/channel/0029VbB0dRxG8l59MUkoWR29 Amharic Entertainment YouTube www.youtube.com/@fanaentertainment Facebook www.facebook.com/wmccwaltamediaandcommunicationcorporate TikTok www.tiktok.com/@fanamc_entertainment Amharic Podcast YouTube www.youtube.com/@fanamcpodcast በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡ ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስለሆኑ እናመሰግናለን!