የሀገር ውስጥ ዜና

የጣና ሐይቅን ደህንነት ለመጠበቅ የወጡ ሕጎች በተጠናከረ ሁኔታ እንዲተገበሩ ተጠየቀ

By Hailemaryam Tegegn

August 17, 2025

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 11፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የጣና ሐይቅን ደህንነትና የብዝኀ ህይወት ሃብቶችን ለመጠበቅ የወጡ ሕጎች በተጠናከረ ሁኔታ እንዲተገበሩ ተጠየቀ፡፡

የአማራ ክልል የአካባቢና ደን ጥበቃ ባለስልጣን የጣና ሐይቅ ደህንነትን በተመለከተ ከተለያዩ ድርጅቶች፣ በሐይቁ ዙሪያ ከሚገኙ ሆቴሎች፣ የሀይማኖት ተቋማትና ባለድርሻ አካላት ጋር ምክክር አካሂዷል፡፡

የጣና ሐይቅ የአካባቢና የውሃ ብክለት፣ ደለልና መጤ አረሞች፣ የደኖች መመናመንና ሌሎች ስጋቶች እንዳለበት በውይይቱ ላይ ተነስቷል።

ለሐይቁ ደህንነት መሰረት የሆኑና በዙሪያው የሚገኙ ውሃ አዘል ቦታዎችን በአግባቡ መጠበቅ እንዳልተቻለም ነው የተመላከተው፡፡

በውይይቱ ላይ ተሳታፊ የሆኑ ድርጅቶችና ባለድርሻ አካላት የሐይቁን ወሰኖች ማስከበርና የውሃ አዘል መሬቶችን ደህንነት መጠበቅ እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።

የጣና ሐይቅን ደህንነት ለመጠበቅ የወጡ ህጎችን በተጠናከረ ሁኔታ መተግበር እንደሚገባና ጥፋተኞች ላይ አስተማሪ ርምጃዎች እንዲወሰዱም በመድረኩ ላይ ተጠይቋል፡፡

በደሳለኝ ቢራራ