አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 11፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ሀገራዊ ምክክሩ ችግሮችን በሚያግባባ ሁኔታ በዘላቂነት መፍታት የሚያስችል ነው አሉ የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽነር ብሌን ገብረመድህን፡፡
”የአካል ጉዳተኞች ሚና ለውጤታማ ሀገራዊ ምክክር በኢትዮጵያ” በሚል መሪ ሀሳብ አካል ጉዳተኞችን ያሳተፈ የውይይት መድረክ በባህር ዳር ከተማ እየተካሄደ ነው።
ኮሚሽነሯ በመድረኩ ላይ እንዳሉት ሀገራዊ ምክክሩ መላ ኢትዮጵያውያንን ግልፅ በሆነ መንገድ በማሳተፍ ችግሮችን በሚያግባባ ሁኔታ በዘላቂነት መፍታት የሚያስችል ነው፡፡
በኢትዮጵያ የሚስተዋሉና ላለመግባባት ምክንያት የሆኑ ጉዳዮችን በመለየት ዘላቂነት ባለው መንገድ ተነጋግሮ መፍታት ይገባል ነው ያሉት።
ለዚህ ስኬታማነት አጀንዳ አለን የሚሉ አካላትን ሁሉ በማሳተፍ ለምክክር የሚሆኑ አጀንዳዎችን የማሰባሰብ ስራ እየተከናወነ መሆኑን አንስተዋል።
በምክክር ሂደቱ አካል ጉዳተኞች በስፋት እንዲሳተፉ በማድረግ አጀንዳዎቻቸው እንዲካተቱ መደረጉንም ነው ኮሚሽነሯ የገለጹት።
ምክክሩ አሳታፊና አካታች መሆኑን ጠቅሰው፥ በዚህም አካል ጉዳተኞችን ጨምሮ ሴቶች፣ ምሁራን፣ የፖለቲካ ፓርቲ ተወካዮች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የሀይማኖት አባቶችና ሌሎች የማህበረሰብ ክፍሎች መሳተፍቸውን ተናግረዋል።
ለምክክር ሂደቱ የላቀ ውጤታማነት ሁሉም በየዘርፉ ማገዝ የበኩሉን እንዲወጣ ጥሪ ማቅረባቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
በመድረኩ ላይ የአካል ጉዳተኞች ማህበራት ተወካዮችና የሚመለከታቸው አካላት እየተሳተፉ ይገኛሉ።