አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 11፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በአፋር ክልል ወጪን በራስ አቅም መሸፈን የሚያስችሉ የገቢ አማራጮችን በማስፋት አቅም የማጠናከር ስራ እየተከናወነ ነው አሉ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አወል አርባ።
የክልሉ ገቢዎች ቢሮ የ2017 በጀት ዓመት አፈጻጸምና የ2018 ዕቅድን በተመለከተ የዞን፣ የወረዳና የከተማ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች በተገኙበት የውይይት መድረክ ተካሂዷል።
ርዕሰ መስተዳድሩ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፥ በክልሉ በ2018 በጀት ዓመት 8 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር ገቢ ለመሰብሰብ እየተሰራ ነው።
የክልሉን ወጪ በራስ አቅም መሸፈን የሚያስችሉ የገቢ አማራጮችን በማስፋት አቅም የማጠናከር ስራ እየተከናወነ መሆኑንም ነው ርዕሰ መስተዳድሩ ያነሱት፡፡
ገቢን አሟጦ ለመሰብሰብና አቅምን ለማሳደግ በየደረጃው የሚገኙ የሥራ ኃላፊዎች በትጋት እንዲሰሩ አሳስበዋል።
የክልሉ ገቢዎች ቢሮ ኃላፊ አወል አብዱ በበኩላቸው፥ ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ የተከናወኑ የሪፎርም ስራዎች ገቢን ለማሳደግ ያስቻሉ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
በመድረኩ በገቢ አሰባሰብ የተሻለ አፈጻጸም ላስመዘገቡ ወረዳዎች፣ ዞኖችና ከተማ አስተዳደሮች ዕውቅና መሰጠቱን ኢዜአ ዘግቧል።