አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 12፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) መንግስት የቋሚ ደመወዝ ተከፋይ ዜጎችን የኑሮ ጫና ለማቃለል ቁርጠኛ አቋም ይዞ እየሰራ ነው አሉ የገንዘብ ሚኒስትር አሕመድ ሽዴ።
የገንዘብ ሚኒስቴር የመንግስት አገልግሎትና አስተዳደር ሪፎርምን ወደ ሙሉ ትግበራ ማስገባቱን ተከትሎ ከሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን ዕውቅና ተሰጥቶታል።
አቶ አሕመድ ሽዴ በዚህ ወቅት እንዳሉት÷ መንግስት ባለፉት ጥቂት ዓመታት ያካሄዳቸው ዘርፈ ብዙ ሪፎርሞች ተጨባጭ ውጤት አምጥተዋል።
በተለይም የተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ሪፎርሙ የውጭ ምንዛሪ ግኝትን በማሳደግና ኢኮኖሚውን በማነቃቃት ዓይነተኛ ሚና መጫወቱን አንስተዋል።
የውጭ ምንዛሪ ተመን በገበያ እንዲወሰን መደረጉ በተለይም የዝቅተኛ ደመወዝ ተከፋይ ዜጎችን ጫና ውስጥ እንዳይከት መንግስት የተለያዩ ርምጃዎችን እንደወሰደ አስታውሰዋል።
መንግስት የቋሚ ደመወዝ ተከፋይ ዜጎችን የኑሮ ጫና ለማቃለል ቁርጠኛ አቋም ይዞ እየሰራ መሆኑን ጠቅሰው÷ ከመስከረም ጀምሮ የተደረገው ማሻሻያም የዚህ ማሳያ ነው ብለዋል።
የሲቪል ሰርቪስ ኮሚሸን ኮሚሽነር መኩሪያ ኃይሌ (ዶ/ር) በበኩላቸው ÷ የመንግስት ተቋማትን አደረጃጀትና አሰራር በማዘመን በክህሎትና በባህሪ የበቃ የሰው ኃይል አስተዳደርና ልማትን በመዘርጋት ለሕብረተሰብ ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠት የተለያዩ ሪፎርሞች እየተካሄዱ ነው ብለዋል።
የማሻሻያ ሪፎርሙ የገንዘብ ሚኒስቴርን ጨምሮ በስምንት ተቋማት በደረጃ ሲተገበር እንደነበር ነው ያስረዱት፡፡
ከተቋማቱ መካከል የገንዘብ ሚኒስቴር የተለያዩ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎችን ጨርሶ ከዛሬ ጀምሮ ወደ ሙሉ ትግበራ መግባቱን አድንቀዋል።
ከሶስት ነጥብ ሶስት ሚሊየን የመንግስት ሰራተኞች የደመወዝ ማሻሻያ ለማድረግ ተጨማሪ 160 ቢሊየን ብር እንደሚያስፈልግና ይህም የመንግስትን ቁርጠኝነት ያሳያል ብለዋል።
የመንግስት ሰራተኛው ሥራውን በውጤታማነት በመፈፀም ለሀገራዊ ዕድገት የድርሻውን እንዲወጣ መጠየቃቸውንም ኢዜአ ዘግቧል፡፡
ፈጣን እና ወቅታዊ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
YouTube www.youtube.com/@fanamediacorporation Facebook www.facebook.com/fanabroadcasting Telegram t.me/fanatelevision Website www.fanamc.com TikTok www.tiktok.com/@fana_television WhatsApp www.whatsapp.com/channel/0029VbB0dRxG8l59MUkoWR29 Amharic Entertainment YouTube www.youtube.com/@fanaentertainment Facebook www.facebook.com/wmccwaltamediaandcommunicationcorporate TikTok www.tiktok.com/@fanamc_entertainment Amharic Podcast YouTube www.youtube.com/@fanamcpodcast በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡ ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስለሆኑ እናመሰግናለን!