ዓለምአቀፋዊ ዜና

ፕሬዚዳንት ዘለንስኪ ጦርነቱን በፍጥነት ማስቆም ይችላሉ – ትራምፕ

By Hailemaryam Tegegn

August 18, 2025

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 12፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የዩክሬን ፕሬዚዳንት ቮሎዲሚር ዘለንስኪ የሩሲያ ዩክሬን ጦርነትን ማስቆም ይችላሉ አሉ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ፡፡ፕሬዚዳንት ትራምፕ ከዩክሬኑ አቻቸው ጋር በዋሽንግተን ለመነጋገር ከያዙት ቀጠሮ አስቀድሞ አሜሪካ የምታቀርበውን የሰላም ሀሳብ ዩክሬን ትቀበለው ዘንድ ግፊት እያደረጉ መሆኑ ተገልጿል።ከሩሲያ ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን ጋር በአላስካ የነበራቸው ቆይታ ያለ በቂ ስምምነት መቋጨቱን ተከትሎ ፕሬዚዳንት ትራምፕ ከዩክሬን አቻቸው ጋር በዛሬው እለት ለመገናኘት ቀጠሮ ይዘዋል።ፕሬዚዳንት ትራምፕ በማህበራዊ ትስስር ገፃቸው ባስተላለፉት መልዕክት÷ ጦርነቱን ለማስቆም የዩክሬኑ ፕሬዚዳንት ውሳኔ ይጠበቃል ብለዋል፡፡ዘለንስኪ በወሳኝ ነጥቦች ላይ ወደ ስምምነት እንዲመጡ ግፊት እያደረጉ የሚገኙት ትራምፕ÷ በተለይ ክሬሚያ ወደ ዩክሬን ትመለስ እና ዩክሬን የሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃል ኪዳን (ኔቶ) አባል ትሁን የሚሉት ሀሳቦች ለድርድር መቅረብ የለባቸውም ብለዋል፡፡ምርጫው ግልፅ ነው ፕሬዚዳንት ዘለንስኪ በወሳኝ ነጥቦች ከተስማማ ጦርነቱ ይቆማል፤ ካልሆነ ግን ደም አፋሳሹ ጦርነት ይቀጥላል ሲሉ አስጠንቅቀዋል።ፕሬዚዳንት ዘለንስኪ በበኩላቸው÷ ዶናልድ ትራምፕ ጦርነቱን በፍጥነት ለማስቆም ያላቸውን ፍላጎት እንጋራለን ብለዋል።ነገር ግን ዘላቂ ሰላምን የሚያረጋግጥ ስምምነት ላይ መድረስ አስፈላጊ መሆኑን አስምረውበታል።የአውሮፓ ሀገራት መሪዎች በተገኙበት የሚካሄደው የፕሬዚዳንት ትራምፕ እና የፕሬዚዳንት ዘለንስኪ የፊት ለፊት ውይይት ዛሬ ምሽት ይደረጋል፡፡የሁለቱ መሪዎች ውይይት የሩሲያና ዩክሬን ጦርነትን ለማስቆም ወሳኝ ሚና ይኖረዋል መባሉን ሲኤንኤን እና ቢቢሲ ዘግበዋል፡፡በሚኪያስ አየለ