አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 13፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ከፍተኛ የንግድ መስመር የሆነውን የሚኤሶ – ድሬዳዋ የፍጥነት መንገድ ፕሮጀክት አስጀምረዋል፡፡
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፥ የሚኤሶ – ድሬዳዋ የፍጥነት መንገድ መንግሥት የትራንስፖርት ዘርፉን ለማዘመን ያለውን ቁርጠኝነት የሚያንፀባርቅ ነው፡፡
የፍጥነት መንገዱ ለሀገር ውስጥ ታላላቅ የገበያ ዕድሎችን በመፍጠር ንግድና ኢኮኖሚን ከማሳደግ ባሻገር ቀጣናዊ የነጻ ገበያ ግቦችን ከማሳካት አንጻርም ያለው ድርሻ ከፍ ያለ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
የሚኤሶ- ድሬዳዋ የፍጥነት መንገድ የኦሮሚያና ሶማሌ ክልሎችን እንዲሁም ድሬዳዋ ከተማን የሚያስተሳስር ሲሆን፥ የበለጸገች ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ የተያዘው ራዕያችን እውን እየሆነ መምጣቱን የሚያሳይ ወሳኝ አካል ነው ብለዋል፡፡
የሀገሪቱ ትልቁ የንግድ መስመር በሆነው የምሥራቁ ኮሪደር የባቡር መሥመር መዘርጋቱን አስታውሰው፥ ከአማራጭ የፍጥነት መንገዱ ጋር በሚፈጠረው መስተጋብር የተሳለጠ የትራንስፖርት አቅርቦት እንዲኖር ያደርጋልም ብለዋል፡፡
ይህ መንገድ የሚጀመረው ብዙ ባህል በተቀየረበት ጊዜ ነው ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ የመሠረት ድንጋይ አስቀምጦ ጀምሮ መተው፣ አዘግይቶ የሐገር ሀብት ማባከንም ሆነ ከጥራት በታች ሠርቶ መመረቅ እንደማይቻል አስገንዝበዋል፡፡
የፍጥነት መንገዱ ጀመሩትን ሁሉ ማጠናቀቅ ባህል በሆነበት የብልጽግና ዘመን የሚጠናቀቅ ፕሮጀክት መሆኑን ነው የገለጹት፡፡
የሁለቱ ክልሎችና የድሬዳዋ አስተዳደር አመራሮችና ሕዝብ እስካሁን ያደረጉትን ክትትል፣ ድጋፍና አስተዋጽዖ እስከ ፍጻሜው እንዲቀጥሉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
በለይኩን ዓለም