የሀገር ውስጥ ዜና

ለአንጋፋው አርቲስት ደበበ እሸቱ አስከሬን የክብር ሽኝት እየተደረገ ነው

By Mikias Ayele

August 19, 2025

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 13፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የአንጋፋው አርቲስት ደበበ እሸቱ አስከሬን የክብር ሽኝት መርሐ ግብር በብሔራዊ ቴአትር እየተካሄደ ይገኛል፡፡

በሽኝት መርሐ ግብሩ ላይ የአርቲስቱ ቤተሰቦች፣ ወዳጅ ዘመዶች፣ የስራ አጋሮች እንዲሁም አድናቂዎች ተገኝተዋል።

የአርቲስቱን ስራዎች የሚያወሱ እና አርቲስቱን የሚዘክሩ ስነ ስርአቶች በመካሄድ ላይ ናቸው፡፡

የአንጋፋው አርቲስት ደበበ እሸቱ ሥርዓተ ቀብር በዛሬው ዕለት 8:00 ላይ በመንበረ ፀባኦት ቅድስት ስላሴ ካቴድራል ይፈጸማል።

ባደረበት ሕመም በሕክምና ሲረዳ ቆይቶ ከትናንት በስቲያ ከዚህ ዓለም በሞት የተለየው አንጋፋው አርቲስት ደበበ እሸቱ በኢትዮጵያ ኪነ ጥበብ ዘርፍ የላቀ አስተዋጽኦ ያበረከተ ሲሆን÷ በሬዲዮ፣ በቴሌቪዥን፣ በፊልም እና በጋዜጠኝነት ሙያ በርካታ ሥራዎችን ለአድማጭ ተመልካች አቅርቧል፡፡

ደራሲ፣ ተርጓሚ፣ አዘጋጅ እና ተዋናይ ሆኖ ለረጅም ዓመታት ያገለገለው አርቲስቱ ÷ በቴአትር መድረኮች በሕዝብ ዘንድ ተወዳጅ የሆኑ ሥራዎችን በማቅረብ ይታወቃል፡፡

አርቲስት ደበበ በሀገር ፍቅርና በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ (በአሁኑ ብሔራዊ ቴአትር) መድረክ ላይ ለበርካታ ዓመታት በተዋናይነትና በአዘጋጅነት አገልግሏል።

አርቲስት ደበበ መጀመሪያ በቴአትር መድረክ የታየው በመንግስቱ ለማ ያላቻ ጋብቻ ሲሆን÷ በመቀጠልም በሬዲዮ እና ቴሌቪዥን የተለያዩ ሥራዎችን አቅርቧል፡፡

አርቲስቱ ከተሳተፈባቸው ሥራዎች መካከል ያላቻ ጋብቻ፣ ሮሚዮና ዡልየት፣ ጠልፎ በኪሴ፣ ዳንዴው ጨቡዴ፣ ዘ ጌም ኦፍ ቼዝ፣ ኦቴሎ፣ አንድ ዓመት ከአንድ ቀን፣ እናት ዓለም ጠኑ፣ በቀይካባ ስውር ደባ፣ የአዛውንቶች ክበብ፣ የወፍ ጎጆ፣ የቬኒሱ ነጋዴ፣ ማዕበል እና ሌሎች ይገኙበታል፡፡

በተለያዩ ታሪካዊና አዝናኝ ፊልሞች እንዲሁም የቴአትር ሥራዎች አድናቆት የተቸረው አንጋፋው አርቲስት ደበበ እሸቱ÷ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የክብር ዶክትሬት ተሰጥቶታል፡፡

አርቲስቱ ሀገር ችግር ውስጥ በምትሆንበት ጊዜ ከፊት በመቆም በርካታ አስተዋጽኦ ያበረከተ ሲሆን ÷ በበጎ ፈቃድ ሥራዎችም ግንባር ቀደም ነበር፡፡

በሌላ በኩል አርቲስት ደበበ እሸቱ በ1995 ዓ.ም በሀገራዊ ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ ውስጥ በመሳተፍ የምክር ቤት አባል እስከመሆን ደርሷል፡፡

በሶስና አለማየሁ