አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 16፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በአማራ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች ሻደይ፣ አሸንድዬና ሶለል በዓል በድምቀት እየተከበረ ይገኛል።
በዓሉ ላልይበላ፣ ቆቦ እና ሰቆጣ ከተሞችን ጨምሮ በተለያዩ አካባቢዎች የመንግስት የሥራ ኃላፊዎች፣ ጎብኚዎች እና የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች በተገኙበት አብሮነትን ይበልጥ ማጠናከር በሚያስችል መልኩ በመከበር ላይ መሆኑ ተገልጿል።
የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ ባስተላለፉት የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት፤ ባሕል የአንድ ማህበረሰብ ቁሳዊና መንፈሳዊ ትውፊት የሚያንፀባርቅበት የታሪክ አሻራ ነው ብለዋል።
በየዓመቱ በክልሉ በተለያዩ አካባቢዎች የሚከበሩት ባሕላዊና ሐይማኖታዊ በዓላት የማሕበራዊ ግንኙነት ማሳለጫ እሴቶች እንደሆኑም ተናግረዋል።
በአዲስ ዓመት መሸጋገሪያ ወቅት በድምቀት የሚከበሩት የሻደይ፣ አሸንድዬ፣ ሶለል፣ እንግጫ ነቀላ እና ከሴ አጨዳ በዓል ልጃገረዶች ዘንድ በልዩ ልዩ ኩነቶች ደምቀው ይከበራሉ ነው ያሉት።
ልጃገረዶቹ አዲሱን ዘመን በደስታና በሀሴት ለመቀበል በአብሮነት በብሩህ ተስፋ ውስጥ ሆነው በጋራ የሚያከብሩት በዓል መሆኑን ገልጸዋል።
የነጻነትና የአብሮነታቸው ማድመቂያ፤ የመተሳሰብና የፍቅር ማብሰሪያቸው ነው ብለዋል።
በዓሉ አንድነትና የርስ በርስ ትስስርን ለማጠናከር ያለው ሚና ከፍተኛ በመሆኑ ባሕላዊና ሐይማኖታዊ ይዘቱን ጠብቆ ለትውልድ ማቆየት እንደሚያስፈልግ አስገንዝበዋል።
የሻደይ፣ አሸንድዬ፣ ሶለል፣ እንግጫ ነቀላ እና ከሴ አጨዳ በዓል ከሕዝባችን መገለጫነት አልፎ በዓለም ቅርስነት እንዲመዘገብ የተጀመሩ ስራዎችን አጠናክረን እንቀጥላለን ሲሉ አረጋግጠዋል።