የሀገር ውስጥ ዜና

 ያለውን ፀጋ አሟጦ በመጠቀም ከድህነት ለመውጣት መትጋት ይገባል – አቶ አረጋ ከበደ

By Mikias Ayele

August 24, 2025

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 18፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ ያለውን ፀጋ አሟጦ መጠቀም በሚያስችል ስትራቴጂ በመመራት ከድህነት ለመውጣት መትጋት ይገባል አሉ።

የክልሉ የ25 ዓመት አሻጋሪ የዘላቂ ልማት ፍኖተ ካርታ እና የ5 ዓመት ስትራቴጂክ ዕቅድ ላይ ለስምንት ቀናት የሚቆይ ስልጠና ለዞን፣ ለወረዳ እና የከተማ አስተዳደር አመራሮች እየተሰጠ ነው።

ስልጠናው የክልሉን ነባራዊና ታሪካዊ ሁኔታዎች ተንትኖ መረዳት፣ ልማትን ለማስፈን የሰላም ሁኔታውን ማረጋገጥ ላይ መምከር፣ የስትራቴጂክ እቅዱ የማስፈጸሚያ ስልቶችን መረዳት፣ የተግባቦት ሥርዓቱ ላይ መግባባትን ጨምሮ ሌሎች ጉዳዮች ላይ ያተኩራል።

በመድረኩ አቶ አረጋ ከበደ እንዳሉት፤ ዘላቂ ሰላምን መገንባት እና ከድህነት መውጣት የአማራጭ ጉዳይ ሳይሆን የግድ መሆን ያለበት ነው።

ትውልዱ ሥር በሰደደ ድህነት እና ኋላቀርነት እየተሰቃየ ያለውን ሕዝብ ከድህነት ለማውጣት የተመረጠ ነው ብለዋል።

የክልሉ ሕዝብ ድህነት በፈጠራቸው ዘርፈ ብዙ ችግሮች የተተበተበ መሆኑን ገልጸው፤ ያለውን ፀጋ አውቆ እና አሟጦ መጠቀም በሚያስችል ስትራቴጂ ተመርቶ ከድህነት ለመውጣት መትጋት ይገባል ነው ያሉት።

ከ2018 እስከ 2042 ዓ.ም ድረስ ለ25 ዓመታት የሚተገበረውን የክልሉ የልማት ፍኖተ ካርታ ጭብጦች መረዳት አስፈላጊ መሆኑንም አስገንዝበዋል።

ከፍኖተ ካርታው የተቀዳውን የአምስት ዓመት ስትራቴጂክ እቅድ ግለቱን ጠብቆ ሳይቋረጥ መፈጸም የሚያስችል አቅም መፍጠር ያስፈልጋል ብለዋል።

ከተለምዷዊ አሠራር በመውጣትና ለለውጥ በመትጋት የክልሉን እድገትና የሕዝቡን ተጠቃሚነት ማረጋገጥ ልዩ ትኩረት እንደሚፈልግ ገልጸው፤ ለጋራ ሀገራዊ ርዕይ የጋራ አመራርን ማረጋገጥ ያሻል ነው ያሉት።

በደሳለኝ ቢራራ