ዓለምአቀፋዊ ዜና

የሻንጋይ ትብብር ጉባኤ – ከቀጣናዊ ትብብር ባሻገር

By Hailemaryam Tegegn

August 26, 2025

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 20፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የቻይናው ፕሬዚዳንት ሺ ጂንፒንግ ከቀናት በኋላ የሩሲያ አቻቸው ቭላድሚር ፑቲን እና የህንዱን ጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ ጨምሮ ከ20 በላይ ሀገራት መሪዎችንና ከፍተኛ ባለስልጣናትን ይቀበላሉ፡፡

ከመጪው እሁድ ጀምሮ በሰሜናዊ ቻይና በምትገኘው የወደብ ከተማ ቲያንጂን የሚካሄደው 25ኛው የሻንጋይ የትብብር ድርጅት ጉባኤ ደግሞ ለመሪዎቹ መሰባሰብ መልካም አጋጣሚ ሆኗል፡፡

በስድስት አባል ሀገራት ምስረታውን ያደረገው ድርጅቱ በሂደት እየተጠናከረ አሁን ላይ 10 ሀገራትን በአባልነት የያዘ ሲሆን፥ ከቀጣናዊ የሰላምና ጸጥታ ትብብር ባሻገር በተለይም ለደቡባዊ ዓለም ትብብር ምልክት መሆኑ ይነገራል፡፡

በጉባኤው ላይ ከአባል ሀገራቱ በተጨማሪ ሁለት ታዛቢ ሀገራትን ጨምሮ ከእስያ፣ ከመካከለኛው ምስራቅ እና ከአፍሪካ የአጋር ሀገራት መሪዎችና የዓለም አቀፍ ተቋማት ተወካዮች ይሳተፋሉ፡፡

ከጉባኤው ጎን ለጎን በተለይም የሩሲያ፣ ቻይና እና ህንድ መሪዎች የሦስትዮሽ ውይይት እንደሚያደርጉ ይጠበቃል፡፡

ድርጅቱ ሀገራትን ያላገለለ የብዝሃ ዓለም ስርዓትን ማንበር እንደሚያስፈልግ ያለው ጽኑ አቋም፥ ከአባል ሀገራቱ ቀጣናዊ ጉዳይ ባሻገር በተለይም የደቡባዊ ዓለም ትብብርን ዓላማ የሚጋራ ተጠቃሽ ተቋም እንዲሆን አስችሎታል፡፡

ሮይተርስ የደቡባዊ ዓለም ጠንካራ የትብብር ምልክት ሲል የገለጸው የቲያንጂኑ ሁነት፥ በአዲስ የትብብር እሳቤ የተቃኘ የዓለም አቀፍ ግንኙነት ለመፍጠር የጎላ ሚና እንዳለው የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርን መግለጫ ጠቅሶ ዘግቧል፡፡

ቀጣናዊ የጸጥታና ደህንነት ትብብር ብሎም ሽብርተኝነትን በጋራ መዋጋትን መነሻ ያደረገው የሻንጋይ ትብብር ድርጅት፥ አሁን ላይ ወደ ዓለም አቀፍ የኢኮኖሚ ትብብር እየተሻገረ መምጣቱንም አመልክቷል፡፡

በሁነቱ ላይ በቀጣይ 10 ዓመታት ገቢራዊ የሚደረግ ስትራቴጂ እንደሚጸድቅ የሚጠበቅ ሲሆን፥ የተባበሩት መንግስታት 80ኛ ዓመት ምስረታ የሚታሰብባቸው ዝግጅቶች መካተታቸውም ነው የተገለጸው፡፡

በኃይለማርያም ተገኝ