አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 22፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በአማራ ክልል በሁለተኛ ዙር ከ6 ሺህ በላይ የቀድሞ ታጣቂዎችን ወደ ተሃድሶ ስልጠና የማስገባት ሥራ ተጀመሯል፡፡
በብሔራዊ ተሃድሶ ኮሚሽን የደብረ ብርሃን ጊዜያዊ ተሃድሶ ስልጠና ማዕከል በሰሜን ሸዋ ዞንና ደብረብርሃን ከተማ ለቀድሞ ታጣቂዎች በዛሬው ዕለት የተሃድሶ ስልጠና መስጠት ጀምሯል።
የብሔራዊ ተሃድሶ ኮሚሽን ኮሚሽነር ተመስገን ጥላሁን በዚህ ወቅት እንዳሉት ÷ ከ72 ሺህ በላይ የቀድሞ ታጣቂዎችን በትግራይ፣ ኦሮሚያ፣ አፋር እና አማራ ክልሎች በማሰልጠን መልሶ የማቋቋም ሥራ እየተከናወነ ነው።
በአማራ ክልል ብቻ በመጀመሪያው ዙር ከ5 ሺህ በላይ የመንግስትን የሰላም ጥሪ የተቀበሉ የቀድሞ ታጣቂዎችን ማስልጠን መቻሉን ነው ያስረዱት፡፡
በ2ኛው ዙር በደብረ ብርሃን፣ ኮምቦልቻና ጎንደር ማዕከላት ከ6 ሺህ በላይ የቀድሞ ታጣቂዎች ከዛሬ ጀምሮ የተሃድሶ ስልጠና እንደሚወስዱ ተናግረዋል፡፡
የሰላም ዋጋው የማይተካ በመሆኑ በየትኛውም አካባቢ በትጥቅ ትግል ውስጥ የሚገኙ ዜጎች ወደ ሰላማዊ ውይይት እንዲመጡም ጥሪ አቅርበዋል፡፡
የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዴዔታ ተስፋሁን ጎበዛይ በበኩላቸው ፥ ሠላም ልማትን ለማረጋገጥ አማራጭ የሌለው አውድ መሆኑን አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡
ወደ ሠላማዊ አማራጭ ለሚመጡ ታጣቂዎች መንግስት አሁንም ከግማሽ በላይ ተጉዞ እንደሚቀበልም አረጋግጠዋል፡፡
ልዩነቶችን በቃታ መሳሳብ ሳይሆን በሃሳብ ልዕልና ለመፍታት ሁሉም የበኩሉን ሊወጣ እንደሚገባም አስገንዝበዋል፡፡
በወንድሙ አዱኛ