ስፓርት

የጥሩ ስብዕና ባለቤቱ አሰልጣኝ ቶማስ ቱሄል …

By Abiy Getahun

August 29, 2025

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 23፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በዓለም ላይ አሉ ከሚባሉ ምርጥ አሰልጣኞች መካከል አንዱ ነው ጀርመናዊው የእንግሊዝ ብሄራዊ ቡድን አሰልጣኝ ቶማስ ቱሄል፡፡

ቶማስ ቱሄል በአሰልጣኝነት ዘመኑ በክለብ ደረጃ ኦግስበርግ፣ ሜይንዝ 05፣ ቦርሺያ ዶርትሙንድ፣ ባየርን ሙኒክ፣ ፒኤስጂ እና ቼልሲን ማሰልጠኑ ይታወሳል፡፡

ከቼልሲ ጋር የአውሮፓ ሻምፒየንስ ሊግ እና ሱፐር ካፕ ዋንጫን ያሳካው አሰልጣኙ በቼልሲ ቆይታው የፊፋ የዓመቱ ምርጥ አሰልጣኝ ተብሏል፡፡

የተለያዩ ክለቦችን ማሰልጠን የቻለው ቱሄል በፈረንሳዩ ክለብ ፒኤስጂ ቆይታው ፒኤስጂን በፈረንጆቹ 2020 ለአውሮፓ ሻምፒየንስ ሊግ ፍጻሜ ማብቃት ቢችልም በጀርመኑ ክለብ ባየርን ሙኒክ ተሸንፎ ዋንጫውን ማጣቱ አይዘነጋም፡፡

አሰልጣኝ ቶማስ ቱሄል በተጫዋቾች፣ በዙሪያው ባሉ ሰዎች እንዲሁም በደጋፊዎች ጭምር ባህሪው ይወደዳል። በተለይም በምዕራብ ለንደኑ ክለብ ቼልሲ ደጋፊዎች ዘንድ ልዩ ክብር አለው ።

ጀርመናዊው የወቅቱ የእንግሊዝ ብሄራዊ ቡድን አሰልጣልኝ ቶማስ ቱሄል ሰብዓዊነትን የተላበሰ ስለመሆኑም ተግባሩ ይመሰክራል።

የአሰልጣኙን ደግነት ከሚያሳዩ አጋጣሚዎች መካከል ከፒኤስጂ ጋር ሲለያይ እና ፓሪስን ሲለቅ ያደረገው በጎ ተግባር ከስሙ ጋር ሁሌም ይነሳል፡፡

በሜዳ ላይም ሆነ ከሜዳ ውጭ ጥሩ ስብዕናን የተላበሰ እንደሆነ የሚነገርለት ቱሄል ፓሪስን ሲለቅ የመኖሪያ ቤቱን ፅዳት የምትጠብቅ ከፊሊፒንስ ለመጣችው የጽዳት ባለሙያ በዋለው ውለታ ሁሌም በብዙዎች ይወደሳል፡፡

ልጅቷ በፓሪስ የሚገኘውንና ቱሄል ከቤተሰቦቹ ጋር የሚኖርበትን መኖሪያ ቤት በጥሩ ሁኔታ በመያዝና ያለድካም ስራዋን በአግባቡ በመከወን ምስጉን ነበረች።

በጊዜ ሂደትም በቱሄል ቤተሰብ ዘንድ ተወዳጅ ከመሆን አልፋ ከቤተሰቡ ጋር ጠንከር ያለ ግንኙነት መፍጠር ቻለች፡፡

የልጆች እናት የሆነችው ባለሙያዋ አንዱ ልጇ በልብ ህመም ምክንያት ከፍተኛ ወጪ የሚጠይቅ የልብ ቀዶ ህክምና ማድረግ እንዳለበት በሐኪሞች ይነገራታል።

ልጇን ለማዳን የምታደርገው ጠፍቶባት በነበረ ጊዜም ቶማስ ቱሄል ያለምንም ማቅማማት ሙሉ የህክምና ወጪውን በመሸፈን ልጁ የልብ ቀዶ ህክምናውን እንዲያደርግ እና ታክሞ እንዲድን በማድረግ በጎ ተግባር መፈፀሙ አይዘነጋም፡፡

ቱሄል ፓሪስ ከተማን ከመልቀቁ እና ወደ ቼልሲ ከመምጣቱ በፊት የጽዳት ባለሙያዋን ልጅ ከማሳከም ባለፈ ፊሊፒንስ ውስጥ እጅግ ዘመናዊ ቤት ገዝቶ በስጦታ አበርክቶላታል፡፡

ፊሊፒንስ ውስጥ ቤት ከገዛላት በኋላም ወደ ሀገሯ ተመልሳ ሄዳ ከልጆቿ ጋር እንድትኖር እድሉን አመቻችቷል ።

ይህ በሜዳ ላይም ሆነ ከሜዳ ውጭ ጥሩ ስብዕናን የተላበሰው አሰልጣኝ ቶማስ ቱሄል በፈረንጆቹ 1973 ነሐሴ 29 ቀን በዛሬዋ ዕለት ነበር የተወለደው፡፡

በወንድማገኝ ፀጋዬ