የሀገር ውስጥ ዜና

በአማራ ክልል በርካታ ታጣቂዎች የሰላም አማራጭን መቀበል ጀምረዋል

By Mikias Ayele

August 29, 2025

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 23፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የአማራ ክልል ሰላምና ፀጥታ ቢሮ በርካታ ታጣቂ ሀይሎች የሰላም አማራጭን በመቀበል ወደ ተሃድሶ ማዕከላት እየገቡ ነው አለ፡፡

የቢሮው ምክትል ኃላፊ አቶ በሪሁን መንግስቱ በሰጡት መግለጫ÷ በክልሉ ከተለያዩ አካባቢዎች በምህረት የገቡ የቀድሞ ተዋጊዎች ወደ ጎንደር ጊዜያዊ የተሃድሶ ስልጠና ማዕከል መግባት ጀምረዋል።

ከነገ ጀምሮ የተሃድሶ ስልጠና ለመስጠት አስፈላጊው ቅድመ ዝግጅት ተደርጓል ብለዋል።

የተሃድሶ ስልጠናው የሚሰጠው በአማራ ክልል መንግስት እና በብሔራዊ ተሃድሶ ኮሚሽን ትብብር መሆኑን ገልፀዋል፡፡

መንግስት የጀመረውን የሰላም ሂደት ለማሳካት ህብረተሰቡ ድጋፍ ማድረግ እንዳለበት ገልጸው÷ የቀድሞ ተዋጊዎች ወደ መደበኛ ኑራቸው እንዲመለሱ የተጠናከረ ድጋፍ ይደረጋል ነው ያሉት።

ታጣቂዎች የሰላም አማራጭን እንዲቀበሉ የተለያየ ጥረት ሲደረግ መቆየቱ በማንሳት÷ በሰለጠነ መንገድ ችግሮችን በውይይት የመፍታት ባህልን ማሳደግ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

በምናለ አየነው