የሀገር ውስጥ ዜና

የአፍሪካን ትርክት በአፍሪካዊ ቅኝት ለዓለም መግለጥ ይገባል

By Mikias Ayele

August 29, 2025

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 23፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የጋዜጠኝነት እና ሥነ ተግባቦት ምሁራን የአፍሪካን ትርክት በአፍሪካዊ ቅኝት፤ በአፍሪካውያን አንደበት ለዓለም ህዝብ መግለጥ ይገባል አሉ።

ፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን ከቻይና ኮሙኒኬሽን ዩኒቨርሲቲ እና ከፓን አፍሪካን ኮንስትራክቲቭ ጆርናሊዝም ኢኒሼቲቭ ጋር በመተባበር ያዘጋጀዉ ዓለም አቀፍ ጉባኤ በአዲስ አበባ ተካሂዷል።

የፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፈፃሚ አማካሪ ዳዊት መሰፍን በመድረኩ እንዳሉት÷ መገናኛ ብዙሃን ችግርን ከነ መፍትሄው፤ ጉድለትን ከነ መንስኤው መጠቆም ላይ አተኩረዉ መስራት አለባቸው።

መገናኛ ብዙሃኑ በዚህ መሰረት ከሰሩ የሀገርን ሙሉ መልክ ማሳየት እንደሚችሉ አስረድተዋል።

በቻይና ኮሙኒኬሽን ዩኒቨርሲቲ የዓለም አቀፍ ግንኙነት መመህርና ተመራማሪ ዣንግ ያግንቺዉ (ፕ/ር)፤ ጠንካራና የበለጸገች ቻይናን እውን በማድረግ ሂደት መገናኛ ብዙሃን ገንቢ ሚና ነበራቸዉ ብለዋል።

የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን አድነትን በሚያፀኑ፣ የህዝብን አብሮነት በሚያጠናክሩ እና ብሔራዊ ጥቅምን በሚያስከብሩ አጀንዳዎች ላይ የጋራ አቋም መያዝ እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።

በዚህም ለሀገር ግንባታ ትልቅ እገዛ ማድረግ ይችላሉ ነው ያሉት።

በመድረኩ የተሳተፉ የኢትዮጵያ፣ ታንዛኒያ፣ ቻይና እና የተለያዩ ሀገራት ዩኒቨርሲቲዎች ምሁራን በበኩላቸው፤ የአፍሪካን ትርክት በአፍሪካዊ ቅኝት፤ በአፍሪካውያን አንደበት ለዓለም ህዝብ መግለጥ እንደሚገባ ተናግረዋል።

ለዚህም ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ መገናኛ ብዙሃን እና ጋዜጠኞችን ማፍራት እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል።

መገናኛ ብዙሃኑ ከነባራዊ ሁኔታቸው እና ከደረሱበት የእድገት ደረጃ ጋር የሚጣጣሙ የጋዜጠኝነት ስልቶችን በመቀመርና በመተግበር ውጤታማ ሊሆኑ እንደሚችሉ ተመላክቷል፡፡