የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤው አፍሪካዊ  መፍትሔዎችን ለማፈላለግ ከፍተኛ ሚና ይኖረዋል – ፍፁም አሰፋ (ዶ/ር)

By Mikias Ayele

August 29, 2025

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 23፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የፕላንና ልማት ሚኒስትር ፍፁም አሰፋ (ዶ/ር) በአዲስ አበባ የሚካሄደው 2ኛው የአፍሪካ አየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ ለአፍሪካዊ የአየር ንብረት ለውጥ ችግሮች አፍሪካዊ መፍትሔ ለማፈላለግ ከፍተኛ ሚና ይኖረዋል አሉ፡፡

ሚኒስትሯ ጉባኤውን አስመልክተው ከፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን ጋር ባደረጉት ቆይታ÷ የአየር ንብረት ለውጥን በተመለከተ ቀጠናዊ፣ አህጉራዊ እና ዓለም አቀፋዊ ጉባኤዎች እንደሚደረጉ አንስተዋል፡፡

በኢትዮጵያ የሚደረገው ጉባኤ አፍሪካውያን መሪዎች በአህጉር አቀፍ የአየር ንብረት ለውጥ ላይ በመወያየት የመፍትሔ ሀሳቦችን የሚያፈላልጉበት መድረክ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

አፍሪካ በአየር ንብረት ለውጥ ሳቢያ ለሚከሰቱ አደጋዎች ተጋላጭ መሆኗን ጠቅሰው፤ ጉባኤው አፍሪካውያን በአየር ንብረት ለውጥ ዙሪያ በትብብር እንዲሰሩ የሚያስችል ነው ብለዋል፡፡

በተጨማሪም ጉባኤው አፍሪካ በ30ኛው የዓለም የአየር ንብረት ለውጥ ጉባዔ ላይ የራሷን ድምፅ ይዛ የምትቀርብበትን ዕድል ይፈጥራል ነው ያሉት።

ኢትዮጵያ በጉባዔው ሀገራዊና አህጉራዊ አጀንዳን በማቅረብ መሪ ተዋናይ እንደምትሆንና የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖን የመከላከል ውጤታማ ተሞክሮዋን እንደምታካፍል አንስተዋል።

አብዛኛው የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤዎች ከሀሳብ ባለፈ ወደ ተግባር አይቀየሩም ያሉት ሚኒስትሯ÷ ኢትዮጵያ ግን የአየር ንብረት ለውጥን በተመለከተ ተጨባጭ ርምጃዎችን እየወሰደች እንደምትገኝ ገልጸዋል፡፡

ለአብነትም ኢትዮጵያ በ2030 የማይበገር አረንጓዴ ኢኮኖሚ ለመገንባት እንዲሁም 20 በመቶውን የአየር ንብረት ለውጥ በጀት በራስ አቅም ለመሸፈን ማቀዷን አመላክተዋል፡፡

በተጨማሪም የካርበን ልቀትን በ2050 ዜሮ ለማድረግ በአረንጓዴ አሻራ እና ታዳሽ ሀይል በትኩረት እየሰራች እንደምትገኝ ተናግረዋል፡፡

ኢትዮጵያ ከአፍሪካ ሕብረት ጋር በመተባበር ሁለተኛውን የአፍሪካ የአየር ንብረት ለውጥ ጉባዔ ከጳጉሜ 3 እስከ 5 ቀን 2017 ዓ.ም በአዲስ አበባ የምታስተናግድ ይሆናል፡፡

በሚኪያስ አየለ