አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 24፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ብሄራዊ የበጎ ፈቃደኛ ወጣቶች አገልግሎት የዜጎችን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮችን እያቀለለ ነው አሉ የሐረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ኦርዲን በድሪ፡፡
በሐረር ከተማ ብሔራዊ የበጎ ፈቃድ ማሕበረሰብ አገልግሎት ሀገራዊ የልምድ ልውውጥ መድረክ እየተካሄደ ነው።
አቶ ኦርዲን በዚሁ ወቅት እንዳሉት ÷ብሄራዊ የበጎ ፈቃደኛ ወጣቶች አገልግሎት ለዜግች ችግር የመፍትሄ አካል በመሆን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮችን እያቀለለ ነው።
የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ሕብረ ብሄራዊ አንድነትን በመገንባት ማሕበራዊ መስተጋብሯ የጠነከረች ኢትዮጵያን ለመገንባት ከፍተኛ ሚና እየተጫወተ ነው ብለዋል።
የዜጎችን የሥራ ባህልና ሀገራዊ የሰላም እሴቶች በማጎልበት ብሄራዊ መግባባትን እውን እያደረገ እንደሚገኝም ጠቁመዋል።
በዚህም በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች የመፍትሄ አካል በመሆን የዜጎችን ችግር እያቀለሉና በክልሉ እየተከናወኑ የሚገኙ የልማት ሥራዎችን እያገዙ መሆኑን ነው ያስረዱት፡፡
በጎ ፈቃደኛ ወጣቶቹ በክልሉ በተለያዩ ማህበራዊ ሥራዎች ላይ በንቃት እየተሳተፉ መሆኑንም የክልሉ ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት ኃላፊ ሔኖክ ሙሉነህ ለፋና ዲጂታል ገልጸዋል፡፡