አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 26፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ከዓባይ በረከት በጭልፋ ልቋደስ ማለት በንጹህ አዕምሮ ቢታይ በምንም መስፈርት ስህተት እና ወንጀል ሊሆን አይችልም አሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ የጉባ ላይ ወግ በሚል ባደረጉት ቃለ ምልልስ÷ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን በተመለከተ የሰው ነገር እንደወሰድን ተደርገን እንጂ የሚገባንን በጣም በጥቂቱ መጠቀም እንደጀመርን አይደለም ብለዋል።
ለሌላ የሚገባ ነገርን ዘርፈን እንደወሰድን፤ ውሃው እንዳይፈስ ገድበው አስቁመውታል የሚሉ እንዳሉ ገልጸው፥ ውሃውን ማስቆም እንደማይቻልና ለማድረግም ግድቡ እንደማይችል አስረድተዋል።
ግድቡ 74 ቢሊየን ሜትሪክ ኪውብ ወይም 74 ትሪሊየን ሊትር ውሃ መያዙን ጠቅሰው፥ ይህም ሆኖ ውሃው አሁንም በመፍሰስ ላይ ይገኛል ነው ያሉት።
ነገር ግን በሰዎች ውስጥ ያለው አመለካከት ትክክለኛ እንዳልነበረ ተናግረዋል።
ዓባይ በዓለም ረዥም ጉዞ የሚጓዝ፤ ክረምት ከበጋ የማይነጥፍ ለሺህ ዓመታት ጉዞውን ያላቋረጠ ውሃ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ ከዚህ በረከት በጭልፋ ልቋደስ ማለት በንጹህ አዕምሮ ቢታይ በምንም መስፈርት ስህተት እና ወንጀል ሊሆን አይችልም ብለዋል።
ዓባይ ማለት ከነስያሜው ትልቅ ስለሆነ ትልቅ ነገር እንደሚጠበቅ ገልጸው፥ የተጀመረው ትንሹ ነገር ማደግ እንዳለበት አመልክተዋል።
ስራችን ትንሹን ነገር ነው እንደጀመርነው እና በዓባይ ተፋሰሰ በርካታ ግድቦችን ሰርተን በርካታ ኢነርጂ አምርተን ሀገራችንን ብቻ ሳይሆን ከባቢውን ልናበራ እንደምንችል ማስረዳት ነበር ብለዋል።
ይሄንን ስናደርግ ደግሞ ለታችኛው ተፋሰስ ሀገራት የሚገባቸውን ውሃ ሳናስቀር፤ በመናበብ መስራት ይቻላል ነው ያሉት።
የተገደበው የዓባይ ወንዝን እንጂ ካርቱም ላይ ናይል የሚለውን ስያሜ የሚያገኘው የናይል ወንዝ እንዳልሆነም ማስረዳታቸውን አመልክተዋል።
ከዚህ በተጨማሪ ደግሞ ዓባይንም ገድበን ለማስቀረት ሳይሆን ኢነርጂ ለማምረት እና በተገቢው መንገድ የሚገባውን ውሃ ማፍሰስ እንደሆነ ጠቁመዋል።
ይሄንን ለማስረዳት ከነበረው ትርክት የተነሳ ብዙ ሰው ያለውን ትክክለኛ መረጃ ለመረዳት እንደሚቸገሩ አስታውሰው÷ ወደ ፊት ግን ለጎብኚዎች ክፍት ሲሆን እና ምን እያልን እንደነበረ ይረዳሉ ሲሉም ነው ያብራሩት።
በዮናስ ጌትነት