ቢዝነስ

በመዲናዋ ለበዓል የሚሆኑ ምርቶች በበቂ ሁኔታ ቀርበዋል – የከተማዋ ንግድ ቢሮ

By Hailemaryam Tegegn

September 04, 2025

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 29፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በአዲስ አበባ ከተማ መጪውን አዲስ አመት ምክንያት በማድረግ ለበዓል የሚሆኑ ምርቶች በበቂ መልኩ ቀርበዋል አለ የከተማዋ ንግድ ቢሮ።

የቢሮው ኃላፊ ወ/ሮ ሀቢባ ሲራጅ በዛሬው ዕለት በሰጡት መግለጫ፥ የከተማዋ ነዋሪዎች ለበዓል አስፈላጊ ምርቶችን በተረጋጋ መልኩ እንዲሸምቱ በቂ አቅርቦት መኖሩን ተናግረዋል፡፡

በከተማዋ ዘጠኝ የመንግስት ገበያ ማዕከላት፣ 219 የቅዳሜና እሁድ ገበያዎች እንዲሁም 20 ባዛሮችን በማዘጋጀት ምርቶች በበቂ መልኩ መቅረባቸውን ጠቁመዋል።

ኃላፊዋ እንዳሉት፥ ከ59 ሺህ በላይ ኩንታል የሰብል ምርቶች፣ ከ124 ሺህ በላይ የዳልጋ ከብት፣ ከ289 ሺህ በላይ በግ እና ፍየል እንዲሁም ከ698 ሺህ በላይ ዶሮ ለገበያ ቀርቧል፡፡

በዓሉን አስመልክቶ ህገወጥ የምርት ክምችት፣ በምርቶች ላይ ባዕድ ነገር የሚቀላቅሉ ነጋዴዎችን እና መሰል ህገወጥ የንግድን እንቅስቃሴዎችን ለመከላከል ክትትልና ቁጥጥር እንደሚደረግ አስጠንቅቀዋል፡፡

ቅድስት ተስፋዬ