የሀገር ውስጥ ዜና

ታላቁ የህዳሴ ግድብ በመጠናቀቁ ትልቅ ኩራት ተሰምቶናል – የሚዲያ አንቂዎች

By Hailemaryam Tegegn

September 04, 2025

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 29፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በመጠናቀቁ ትልቅ ኩራት ተሰምቶናል አሉ የሚዲያ አንቂዎች፡፡

ከፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን ጋር ቆይታ ያደረጉት ኡስታዝ ጀማል በሽር፥ የህዳሴ ግድብ መጠናቀቅ የተፈጥሮ ሀብት የመጠቀም ነጻነታችንን ያወጅንበት ነው ብለዋል።

ኢትዮጵያዊያን ባለፉት ስድስት ዓመታት በግድቡ ዙሪያ የሰሩት ስራ ግብፅ ላለፉት 70 ዓመታት ስለ ኢትዮጵያና አባይ ወንዝ የሰራችውን ሀሰተኛ ፕሮፓጋንዳ በመመከት እውነታውን ለዓለም ያሳየ መሆኑን ተናግረዋል።

በተለያዩ ቋንቋዎች የህዳሴ ግድብን እውነታ ለዓለም በማሳወቃቸውና ለፍሬ በቅቶ በመመልከታቸው ትልቅ ኩራት እንደተሰማቸውም ነው የተናገሩት፡፡

ጋዜጠኛ ፈኢድ መሐሙድ በበኩሉ የህዳሴ ግድብን በተመለከተ በተለያዩ ዓለም አቀፍ ቋንቋዎች የተሰሩ የሚዲያ ስራዎች ትልቅ አስተዋፅኦ እንደነበራቸው ጠቁሟል፡፡

በተለይም በአረብኛ ቋንቋ የህዳሴ ግድብ እውነታዎችን ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በተለያዩ ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃን የማሳወቅ ስራዎች መሰራታቸውን አስታውሷል፡፡

ፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽንን ጨምሮ በተለያዩ መገናኛ ብዙኃን የአረብኛ ቋንቋ አገልግሎት መጀመሩ ትክክለኛ መረጃዎችን ለዓለም ለማሳወቅ ትልቅ ድርሻ ይኖረዋልም ነው ያለው፡፡

በቀጣይም ህዳሴ ግድብን ጨምሮ ኢትዮጵያን የሚመለከቱ ሀሰተኛ መረጃዎችን የማጋለጥ ስራዎችን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ አረጋግጠዋል።

በዙፋን ካሳሁን