አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 30፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን እና የግብፅ ብሄራዊ ቡድን በ3ኛው የአፍሪካ ዋንጫ የፍጻሜ ጨዋታ ላይ መገናኘታቸው ይታወሳል፡፡
ኢትዮጵያ ካዘጋጀቻቸው የአፍሪካ ዋንጫ ጨዋታዎች መካከል ሶስተኛው የአፍሪካ ዋንጫ ተጠቃሽ ነው፡፡
ሁለቱ ብሄራዊ ቡድኖች በአዲስ አበባ ስታዲየም ባደረጉት 3ኛው የአፍሪካ ዋንጫ የፍጻሜ ጨዋታ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ድል በማድረግ ዋንጫውን ማንሳቱ አይዘነጋም፡፡
የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ግብፅን አሸንፎ ዋንጫውን ያሳካበት ታሪካዊው 3ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ብዙ ገጠመኞችንም አስተናግዷል፡፡
ኢትዮጵያ 3ኛውን የአፍሪካ ዋንጫ አዘጋጅታ ዋንጫውን ያነሳች ሲሆን ÷ በውድድሩ ኢትዮጵያ፣ ግብፅ፣ ቱኒዚያ እና ዩጋንዳ ተሳትፈዋል፡፡
የግብፅ ብሄራዊ ቡድን በ3ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ተሸንፎ ዋንጫውን ካጣ በኃላ የቡድኑ ተጫዋቾች ለሽንፈታቸው የተለያዩ ምክንያቶችን አቅርበዋል።
በዋናነት በ3ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ለመሸነፋቸው ምክንያት አድርገው ያቀረቡት ከምንበላው ምግብ ጋር መድኃኒት ቀላቅለው ስለሰጡን ነው የሚለው ይገኝበታል።
ከዩጋንዳ ጋር የመጀመሪያውን ጨዋታ አድርገው ከጨረሱ በኃላ ይመርዙናል ብለው ፈርተው ምግብ ከአምባሳደራቸው መኖሪያ ቤት እያመጡ ሲመገቡ ቆይተዋል፡፡
ግብጾች ከዋንጫው ጨዋታ አስቀድሞ ጥንቃቄ ከማድረግ ባለፈ የብሄራዊ ቡድኑ ተጫዋቾች ለሚያቀርቧቸው ጥያቄዎች በብርሃን ፍጥነት ምላሽ ይሰጡ ነበር፡፡
ግብጾች እንደ ቅሬታ ያቀረቧቸው ምክንያቶች አሳማኝ ያልነበሩ እና በግማሽ ፍጻሜ ከዩጋንዳ ጋር በመጫወታቸውም ደስተኛ እንዳልነበሩ ሲገልጹ ቆይተዋል፡፡
በግማሽ ፍጻሜው ከዩጋንዳ ጋር ባደረግነው ጨዋታ አቅማችንን በመጨረሳችን በዋንጫው ጨዋታ ደካማ እንቅስቃሴ ለማድረግ እና ተዳክመን ለመታየት ተገደናል ብለዋል፡፡
በ3ኛው አፍሪካ ዋንጫ የፍጻሜ ጨዋታ የተሸነፈው እና ዋንጫውን በኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን የተነጠቀው የግብፅ ብሄራዊ ቡድን በፍጻሜ ጨዋታው ዕለት ኢትዮጵያ ባዘጋጀችው ኳስ አንጫወትም እስከማለት ደርሰዋል፡፡
ያም ሆኖ ራሳቸው ግብጾች በመረጡት ኳስ የተካሄደው የፍጻሜ ጨዋታ በኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን አሸናፊነት ነበር የተጠናቀቀው፡፡
በእነዚህ ምክንያቶች ያልተደሰቱት ግብፆች ኢትዮጵያዊያን ተጫዋቾች የሚጫወቱት አጨዋወት ጉልበት የበዛበት ስለሆነ የእኛን ተጫዋቾች ይጎዱብናል ብለው ክስ በማቅረባቸው የዋንጫው ጨዋታ ከመጀመሩ በፊት የመሃል ዳኛው የኢትዮጵያን ተጫዋቾች እስከማስጠንቀቅም ደርሰው ነበር፡፡
ግብጾች ከፍጻሜው ጨዋታ አስቀድሞ ብዙ ምክንያቶችን ቢደረድሩም የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን 3ኛውን የአፍሪካ ዋንጫ ከማሸነፍ ያገደው ሃይል አልነበረም፡፡
ሁለቱ ብሄራዊ ቡድኖች ታሪካዊ ተቀናቃኝነታቸው ዘመናትን የተሻገረ ሲሆን ÷ ዛሬ ምሽት ደግሞ በዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታ በብርቱ ይፋለማሉ፡፡
የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ባህሩ ጥላሁን ከዛሬው ጨዋታ አስቀድሞ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ÷ “ትልቅ የታሪክ አሻራ ያስቀመጥንበት የሕዳሴ ግድብ በሚመረቅበት ሰዓት የሚደረግ ጨዋታ በመሆኑ ትልቅ ትርጉም የሚሰጠው ነው” ብለዋል፡፡
ዋልያዎቹ ዛሬ ነሐሴ 30 ቀን 2017 ዓ.ም ካይሮ ላይ ከፈርኦኖቹ ጋር የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታቸውን ምሽት 4 ሰዓት ላይ የሚያደርጉ ይሆናል፡፡
በወንድማገኝ ጸጋዬ