የሀገር ውስጥ ዜና

የኢትዮጵያን ፀጋ ለዓለም ለማስተዋወቅ ጉልህ ሚና ያለው ኪን-ኢትዮጵያ

By Yonas Getnet

September 05, 2025

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 30፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዴኤታ ተስፋሁን ጎበዛይ ኪን-ኢትዮጵያ የጥበብና ባህል ጉዞ የኢትዮጵያን ፀጋ ለዓለም ለማስተዋወቅ ጉልህ ሚና አለው አሉ።

በሩሲያ የሚደረገውን ሁለተኛው የኪን ኢትዮጵያ ጉዞ በተመለከተ የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት እና የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር ከሻኩራ ፕሮዳክሽን ጋር በመሆን መግለጫ ሰጥተዋል።

አቶ ተስፋሁን ጎበዛይ በመግለጫው እንዳሉት፤ ኪን-ኢትዮጵያ የጥበብና ባህል ጉዞ ኢትዮጵያን በልኳ ለዓለም የማስተዋወቅ ዓላማ አለው።

እንዲህ ዓይነት የጥበብና ባህል ጉዞ በህዝብ ለህዝብ ግንኙነትና ፐብሊክ ዲፕሎማሲ ስራዎች ውስጥ አስፈላጊ ከሆኑ ጉዳዮች መካከል አንዱ ነው ብለዋል።

ከዚህ በፊት ለሶስት ቀናት በቻይና ቆይታ የነበረው ኪን- ኢትዮጵያ በሀገራቱ መካከል ያለውን የመንግስት ለመንግስት ግንኙነት በህዝብ ለህዝብ ትስስር ለማጠናከር አስተዋጽኦ ማበርከቱን ተናግረዋል።

ጉዞው በሀገር ውስጥና በዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን ሽፋን ያገኘ ሁነት እንደነበር አስታውሰዋል።

ጉዞው የኢትዮጵያን የኢንቨስትመንት አማራጭ ለማስተዋወቅ እድል የፈጠረ እና ቀጣይነት ያለው የህዝብ ለህዝብ ትስስር፣ ንግድና ኢንቨስትመንት ልውውጥ የሚያናክር እንደሆነ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያን መልክ ለዓለም በማስተዋወቅ ረገድም ትልቅ ሚና እየተጫወተ ነው ብለዋል።

የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ዴኤታ ነብዩ ባዬ (ረ/ፕ) በበኩላቸው፤ 2ኛው የኪን ኢትዮጵያ ጉዞ ከጳጉሜ 4 ቀን 2017 እስከ መስከረም 5 ቀን 2018 ዓ.ም በሩሲያ ይካሄዳል ብለዋል።

በሞስኮ ሴንት ፒተርስበርግና በሚካሄደው የጥበብ ትዕይንት የተለያዩ ሁነቶች እንደሚካሄዱ ገልጸው፤ የኢትዮጵያና ሩሲያን የባህል ትስስር የበለጠ ለማጠናከር እንደሚያግዝ ጠቁመዋል።

በሩሲያ በሚካሄደውና ከ60 በላይ ሀገራት የባህልና ጥበብ ተወካዮች በሚሳተፉበት የዩናይትድ ካልቸራል ፎረም ላይ በጉዞው የሚሳተፈው የኪን ኢትዮጵያ ቡድን የተለያዩ ትዕይንቶችን እንደሚያቀርብም ነው የተናገሩት።

በዮናስ ጌትነት

ፈጣን እና ወቅታዊ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

YouTube www.youtube.com/@fanamediacorporation Facebook www.facebook.com/fanabroadcasting Telegram t.me/fanatelevision Website www.fanamc.com TikTok www.tiktok.com/@fana_television WhatsApp www.whatsapp.com/channel/0029VbB0dRxG8l59MUkoWR29 Amharic Entertainment YouTube www.youtube.com/@fanaentertainment Facebook www.facebook.com/wmccwaltamediaandcommunicationcorporate TikTok www.tiktok.com/@fanamc_entertainment Amharic Podcast YouTube www.youtube.com/@fanamcpodcast በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡ ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስለሆኑ እናመሰግናለን!