አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 30፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ በአማራ ክልል የመስኖ ልማት ስራዎችን በአግባቡ ለማስተዳደር የሚያስችል ዲጂታል ስርዓት ይፋ አደረገ፡፡
ዩኒቨርሲቲው ከክልሉ የመስኖና ቆላማ አካባቢዎች ልማት ቢሮ ጋር በመተባበር ያዘጋጀውን የመስኖ ሥራዎች ዲጂታል ስርዓት በተመለከተ አውደ ጥናት አካሂዷል።
የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት መንገሻ አየነ (ዶ/ር) በዚሁ ወቅት እንዳሉት፥ የዲጂታል ስርዓቱ በሀገር አቀፍ ደረጃ ዘመናዊ የመስኖ አስተዳደር ሥርዓትን የሚያስተዋውቅ ነው።
የመስኖ ግድቦች ደህንነት መረጃ ለማግኘት፣ የማምረት አቅማቸውን ለማወቅ፣ በመስኖ የመልማት አቅም ያላቸውን አካባቢዎች ለማሳየትና ተያያዥ ሥራዎችን ለማመላከት ያስችላልም ነው ያሉት፡፡
የክልሉ መስኖና ቆላማ አካባቢዎች ልማት ቢሮ ኃላፊ ዳኝነት ፈንታ (ዶ/ር) በበኩላቸው፥ የዲጂታል ስርዓቱ በትክክለኛ መረጃ ላይ ተመስርቶ ውስን የሆነውን የውሃ ሃብት በአግባቡ ለመጠቀም ያስችላል ብለዋል።
በክልሉ 2 ነጥብ 2 ሚሊየን ሄክታር በመስኖ የሚለማ መሬት ቢኖርም ከ330 ሺህ ሄክታር በላይ ማልማት እንዳልተቻለ ነው በአውደ ጥናቱ ላይ የተመላከተው።
በክልሉ በ2017 በጀት ዓመት ከ7 ሺህ ሄክታር በላይ ማልማት የሚያስችሉ 176 ፕሮጀክቶች ተጠናቀው ለሥራ ዝግጁ መሆናቸው በመድረኩ ላይ ተነስቷል፡፡
ከ17 ሺህ ሄክታር በላይ ማልማት የሚችሉ ሌሎች 197 ፕሮጀክቶችን የጥናትና ዲዛይን ሥራ ማከናወን ተችሏል ነው የተባለው፡፡
በደሳለኝ ቢራራ