የሀገር ውስጥ ዜና

በአዲስ አበባ ቄራዎች ድርጅት የቀድሞ ስራ አስኪያጅና ምክትል ስራ አስኪያጅ ላይ ክስ ተመሰረተ

By Abiy Getahun

September 05, 2025

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 30፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የማይገባቸውን ጥቅም ለማግኘት ጉቦ በመቀበል በተጠረጠሩት የአዲስ አበባ ቄራዎች ድርጅት የቀድሞ ስራ አስኪያጅ እና ምክትል ስራ አስኪያጅ ላይ ክስ ተመሰረተ፡፡

ተከሳሾቹ፥ የግል ተበዳይ ከአዲስ አበባ ቄራዎች ድርጅት ጋር ያለው ውል እንዲታደስለት ያቀረበውን ጥያቄ ለማስፈጸም 750 ሺህ ብር ጉቦ መቀበላቸው በክሱ ላይ ተመላክቷል፡፡

የክስ መዝገቡን የተመለከተው የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ተረኛ የሙስና ወንጀል ችሎት ነው።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ቄራዎች ድርጅት እና ራኔዝ አድቨርታይዚንግና ሪቴል ዴቨሎፕመንት ሃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር የዳልጋ ከብት ሀሞት ግዥ እና ሽያጭ ውል ተዋውለው ሲሰሩ ቆይተዋል፡፡

የግል ተበዳይ ውል ይታደስልኝ ጥያቄ ያቀረበ ሲሆን፥ 1ኛ ተከሳሽ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ቄራዎች ድርጅት የቀድሞ ስራ አስኪያጅ አቶ ሰይድ ከማል እና 2ኛ ተከሳሽ የድርጅቱ የቀድሞ ምክትል ስራ አስኪያጅ አቶ ዩሴፍ ዲሪብሳ በግላችን ክፍያ ካልከፈላችሁ ውል አናድስም ማለታቸው በክሱ ተመላክቷል፡፡

ተከሳሾቹ በ1996 ዓ.ም የወጣውን የኢፌዴሪ የወንጀል ህግ አንቀጽ 32 ሀ/ለ እና የሙስና ወንጀሎችን ለመደንገግ የወጣውን አዋጅ ቁጥር 881/2007 አንቀጽ 11 እና 2 ስር የተመለከተውን መተላለፋቸውን ዐቃቤ ሕግ በክሱ ላይ አስፍሯል፡፡

በዚህም 1ኛ ተከሳሽ 500 ሺህ ብር እንዲሁም 2ኛ ተከሳሽ 250 ሺህ ብር በመቀበል ከሐምሌ 1 ቀን 2016 ዓ.ም እስከ ሰኔ 30 ቀን 2017 ዓ.ም የሚቆይ የዳልጋ ከብት ግዢና ሀሞት ሽያጭ ውል ተዋውለዋል፡፡

1ኛ ተከሳሽ ዳግመኛ ለእናንተ ውል አንሰጥም እዚህ ግቢ አትገቡም በማለት በማስፈራራት ነሐሴ 18 ቀን 2017 ዓ.ም ከ2ኛ የዐቃቤ ሕግ ምስክር 500 ሺህ ብር ተቀብሎ ሊሄድ ሲል እጅ ከፍንጅ ተይዟል፡፡

2ኛ ተከሳሽ በተለያየ ጊዜ በማስፈራራት በካሽ የተለያየ መጠን ያለው አጠቃላይ 250 ሺህ ብር መቀበላቸውም በክሱ ላይ ተጠቅሷል፡፡

ተከሳሾች ማድረግ የሚገባቸዉን ተግባር ለመፈጸም 750 ሺህ ብር ጉቦ በመጠየቅና በመቀበል በዋና ወንጀል አድራጊነት ተካፋይ በመሆን የማይገባ ጥቅም መቀበል ከባድ የሙስና ወንጀል ተከሰዋል፡፡

ፍርድ ቤቱ ክስ ለመስማት ጥቅምት 6 ቀን 2018 ዓ.ም ቀጠሮ የሰጠ ሲሆን፥ እስከዚያው ተከሳሾች በማረሚያ ቤት እንዲቆዩ ወስኗል።

በመቅደስ ከበደ

ፈጣን እና ወቅታዊ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

YouTube www.youtube.com/@fanamediacorporation Facebook www.facebook.com/fanabroadcasting Telegram t.me/fanatelevision Website www.fanamc.com TikTok www.tiktok.com/@fana_television WhatsApp www.whatsapp.com/channel/0029VbB0dRxG8l59MUkoWR29 Amharic Entertainment YouTube www.youtube.com/@fanaentertainment Facebook www.facebook.com/wmccwaltamediaandcommunicationcorporate TikTok www.tiktok.com/@fanamc_entertainment Amharic Podcast YouTube www.youtube.com/@fanamcpodcast በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡ ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስለሆኑ እናመሰግናለን!