የሀገር ውስጥ ዜና

የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ለሠራተኞችና በጡረታ ለተሰናበቱ አባላቱ ማዕድ አጋራ

By Abiy Getahun

September 05, 2025

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 30፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ለሠራተኞችና በጡረታ ለተሰናበቱ አባላቱ ማዕድ አጋርቷል።

አገልግሎቱ ለፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን በላከው መረጃ እንዳመለከተው፤ ጳጉሜን 2 ቀን 2017 ዓ.ም የሚከበረውን የህብር ቀንና አዲሱን ዓመት ምክንያት በማድረግ ለበአል መዋያ የሚሆን የቁሳቁስ ሥጦታ እና የገንዘብ ድጋፍ አበርክቷል።

በመርሐ-ግብሩ ላይ የተገኙት የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ምክትል ዳይሬክተር ጀነራል አቶ ርስቱ ይርዳው፤ ትናንት ሀገራቸውንና ተቋማቸውን በትጋትና ዋጋ በመክፈል ጭምር ያገለገሉትንና ዛሬም እያገለገሉ የሚገኙትን ሠራተኞች መደገፍ የሰው ተኮር ልማት ሥራችን አካል ነው ብለዋል።

አገልግሎቱ በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት የተጣለበትን ማኅበራዊ ኃላፊነት ለመወጣት ለተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ድጋፍ ማድረጉን አስታውሰው፤ በዛሬው ዕለት የተደረገው የማዕድ ማጋራት መርሐ-ግብርም የዚሁ አካል መሆኑን አመልክተዋል፡፡

የተቋሙ ሠራተኞች ከወር ደመወዛቸው በማዋጣት አቅመ ደካማና አረጋውያን የኅብረተሰብ ክፍሎችን ለመደገፍ የነቃ ተሳትፎ እያደረጉ ነው ብለዋል።

ይህም አገልግሎቱን ከማኅበረሰቡ ጋር ይበልጥ ማስተሳሰሩንና ማኅበራዊ ኃላፊነቱን በሚገባ እንዲወጣ ዕድል መፍጠሩን አመልክተዋል።

የተቋሙ የማኅበረሰብ ተኮር ሥራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉም አረጋግጠዋል።

የአገልግሎቱ ምክትል ዳይሬክተር ጀነራል አቶ ታዜር ገብረእግዚአብሄር በበኩላቸው፤ ተልዕኮአችንን ከመፈጸም ባሻገር የማኅበረሰብ ተኮር የድጋፍ ሥራዎች ላይ ያለን ተሳትፎ እያደገና ባህል እየሆነ መጥቷል ብለዋል፡፡

አገልግሎቱ በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በጎፋ ዞን ገዜ ጎፋ ወረዳ የመሬት መንሸራተት ላጋጠማቸው ዜጎች እና ለመቄዶንያ የአረጋውያን እና የአዕምሮ ሕሙማን መርጃ ማዕከል ድጋፍ ከማድረጉ ባሻገር የተቋሙ ሠራተኞችና የአረጋውያንን መኖሪያ ቤቶች እንዲሁም ትምህርት ቤቶችን በማደስና በመገንባት በኩል ሰፊ ተሳትፎ ማድረጉን ገልጿል።