የሀገር ውስጥ ዜና

የጽናት ቀን በባሕር ዳር ከተማ ተከበረ

By Mikias Ayele

September 06, 2025

አዲስ አበባ፣ ጳጉሜን 1፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በአማራ ክልል ጳጉሜን 1 የጽናት ቀን ‘ጽኑ መሰረት፤ ብርቱ ሀገር’ በሚል መሪ ቃል በባህርዳር ከተማ ተከብሯል፡፡

በዓሉ በወታደራዊ ትርዒት ከማለዳው ጀምሮ ሲከበር የሀገር መከላከያ ሰራዊት፣ የፌዴራል ፖሊስ እና የክልሉ የጸጥታ አካላት ወታደራዊ ትርዒት አሳይተዋል።

ባለፉት ዓመታት ክልሉን ከገባበት ቀውስ ለማውጣት የጸጥታ አካላት የከፈሉት መስዋዕትነት በመርሐ ግብሩ ላይ ተዘክሯል።

በመርሃ ግብሩ የባሕር ዳር ከተማ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ ጎሹ እንዳላማው÷ የውስጥና የውጭ ጠላቶች ተቀናጅተው ኢትዮጵያ በጦርነትና በድህነት አዙሪት እንድትኖር ቢፈርዱባትም ጀግኖች በከፈሉት መስዋዕትነት ህልማቸው ከሽፏል ነው ያሉት።

የጽናት ቀን ሲከበር ጸንተን ሀገራችንን ጠብቀን ያኖርን፣ ለወደፊትም በጽናት የሀገራችንን ሉዓላዊነትና የሕዝባችንን ደህንነት ለማስጠበቅ የምንቆም መሆናችንን የምናሳይበት ነው ብለዋል።

ጠላቶቻችን ያሰመሩልን የጦርነትና የድህነት አዙሪት በብልጽግና ትውልድ ተሰብሯል በማለት ገልጸው÷ በአማራ ክልል የታየው ችግር የተውሶ እንጂ የሕዝባችን ፍላጎትም ዓላማም አይደለም በማለት አስገንዝበዋል።

በደሳለኝ ቢራራ