የሀገር ውስጥ ዜና

የአፍሪካ -ካሪቢያን የጤና ሚኒስትሮች ጉባዔ መካሄድ ጀመረ

By Mikias Ayele

September 06, 2025

አዲስ አበባ፣ ጳጉሜን 1፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የአፍሪካ -ካሪቢያን የጤና ሚኒስትሮች ጉባዔ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው።

በመድረኩ በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ኃላፊ እና የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት አደም ፋራህ እንዳሉት፤ የካሪቢያን ሀገራትና አፍሪካ ወንድማማች ህዝቦች ናቸው፡፡

ኢትዮጵያ የአፍሪካውያን ቤት ብቻ ሳትሆን የዘርዓ አፍሪካውያንም ጭምር ናት ብለዋል፡፡

በዛሬው መድረክ የዲፕሎማሲያዊ ሳይሆን የጋራ ባህልና መዳረሻ ያላቸው ህዝቦች የተገናኙበት እንደሆነም አስገንዝበዋል።

የአፍሪካ እና የካሪቢያን ሀገራት በጤና ዘርፍ በትብብር መስራት አለባቸው ያሉት አቶ አደም÷ ያለንበት ወቅት የህክምና ግብዓቶችን በራስ አቅም በማምረት ራስን ወደመቻል ጉዞ ማቅናት የግድ የሚለን ጊዜ ነው ብለዋል።

የጤና ተደራሽነትን ለሁሉም ህዝቦቻችን የማዳረስ ሀሳብ ጉዳይ ከንግግር ባለፈ ወደተግባር መውረድ ይገባል ነው ያሉት።

የጤና ባለሙያዎቻችንን አቅም በመገንባትና ዘርፉን ዲጂታላይዝ በማድረግ ከዘመኑ ጋር አብሮ መዘመን እንደሚያስፈልግም አስታውቀዋል።

የጤና ሚኒስትር ዶ/ር መቅደስ ዳባ በበኩላቸው÷ የአፍሪካ እና ካሪቢያን የጋራ ድምፅ የዓለም የጤና አስተዳደር ላይ ተፅዕኖ ማሳደር ይችላል ብለዋል።

ይህም በወረርሽኝ ዝግጁነት፣ የፋይናንስ ስርዓት ለውጥ፣ ፍትሀዊ የጤና ቴክኖሎጂ ስርጭት እንዲኖር የሚያደርግ መሆኑን ገልጸዋል።

ከተናጠል እንቅስቃሴ ይልቅ በጋራ መጓዝ ዓላማን ለማሳካት እንደሚያስችል አንስተው፤ የዘርፉን አቅሞች በመጠቀም የተቀናጀና ሁሉንም አቀፍ ሥራ ማከናወን ከተቻለ የጤና ስርዓቱን ከጥገኝነት እንደሚያላቅቅ ጠቁመዋል።

የአፍሪካ እና ካሪቢያን ህዝቦች ክብራቸውን የሚመጥን ጥራት ያለው የጤና አገልግሎት እንዲያገኙ መስራት ይገባል ብለዋል።

 

በአንዷለም ተስፋዬ