አዲስ አበባ፣ ጳጉሜን 2፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) አፍሪካ ለካሪቢያን ሕዝቦች የቤታችን ያክል ነች አሉ የካሪቢያን ሀገራት ዋና ጸሃፊ ካርላ ባርኔት።
2ኛው የአፍሪካ ካሪቢያን ሀገራት መሪዎች ጉባዔ በዛሬው ዕለት በአዲስ አበባ መካሄድ ጀምሯል፡፡
ካርላ ባርኔት በዚህ ወቅት ÷ የአፍሪካና ካሪቢያን ሀገራትን ከባሕልና ሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት በተጨማሪ በርካታ አንድ የሚያደርጉ ትስስሮች እንዳሉ አንስተዋል፡፡
ይህን ዘርፈ ብዙ ትስስር ይበልጥ ማጠናከር እና የጋራ ተጠቃሚነትን ማስረጽ እንደሚገባ አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡
ለዚህም የጋራ ቪዛ ሥርዓት መዘርጋትና በነጻነት ዜጎች የሚንቀሳቀሱበት ሁኔታ መፈጠር ይገባል ነው ያሉት ዋና ጸሃፊዋ።
በጤናው ዘርፍ የተጀመረውን የጋራ ትብብር ማዕቀፍ በሌሎች እንደ ንግድና ኢንቨስትመንት ባሉ ዘርፎች መቀጠል እንደሚያስፈልግም አመልክተዋል፡፡
የተባበሩት መንግስታት ዋና ጸሃፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ ተወካይ አናያ አናንጋ በበኩላቸው÷ የአፍሪካና ካሪቢያን ሀገራት መሪዎች በአንድ ስፍራ መገናኘታቸው ትብብርን ለማጠንከር ጥሩ አጋጣሚ ነው ብለዋል።
ይህን የጋራ ጥምረት የተሻለ ሰላምን መገንባት ወደ ሚቻልበት ደረጃ ማሳደግ የመሪዎች የቤት ሥራ ሊሆን እንደሚገባም አስገንዝበዋል፡፡
ፍትሃዊ ተጠቃሚነትን ለሁለቱም ሕዝቦች ተደራሽ ማድረግ እንዲቻል በጋራ ሁሉን አቀፍ የሆነ ስምምነት መፍጠር ተቀዳሚ ተግባር መሆን እንዳለበት የጉባዔው ተሳታፊዎች አንስተዋል።
በአሸብር ካሳሁን